በአድዋ ያስመዘገብነውን ድል በማስጠበቅ በተባበረ አቅማችን የተሻለች አገር ለመገንባት መሥራት አለብን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

188

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 23/2015 ኢትዮጵያውያን በአድዋ ያስመዘገብነውን ድል በማስጠበቅ በተባበረ አቅማችን የተሻለች አገር ለመገንባት መሥራት አለብን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ለአንድ ዓመት የሚቆይ ሀገር አቀፍ የታክስና የጉምሩክ ሕግ ተገዥነት ንቅናቄ "ግብር ለሀገር ክብር" በሚል መሪ ሃሳብ በዛሬው እለት ተጀምሯል። 

የንቅናቄው ዋነኛ ዓላማም የዜጎችን ግብር የመክፈል ባህል በማሳደግ ለአገር ልማትና እድገት የሚኖራቸውን የላቀ ሚና ማሳደግ መሆኑ ታውቋል። 

በመርሃ-ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅና ከድህነት መውጣት የምንችለው በተባበረ ክንዳችን ሃብቶችን በመጠቀም ማልማት ሲቻል መሆኑን ገልጸዋል። 

በመሆኑም በአድዋ ድል ያሳየነውን አይበገሬነት በተባበረ ክንዳችን አቅማችንን በመጠቀም የተሻለች አገር ለመገንባት መሥራት አለብን ብለዋል። 

የችግሮች ሁሉ መንስኤ የሆነውን የድህነት ቀንበር ለመስበርም በጋራና በትብብር በትጋት ልንሰራ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል። 

የጋራ ሃብቶችን ተጠቅሞ በጋራ ለመልማት ብዙ ጉድለቶች አሉብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ የተሟላ ክብርና ነፃነት እንዲኖራት የራሷን ወጪ በራሷ አቅም መሸፈን አለባት ብለዋል። 

ኢትዮጵያ የእዳ ጫና ያጎበጣት መሆኑን ጠቅሰው፤ እዳዋን በማቃለል የተሟላ ነፃነቷን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በርትተው የሚሰሩላት ወጣቶችና ለተፈጠሩት ዓላማ የሚኖሩ ባለሃብቶች ያስፈልጓታል ብለዋል። 

ኢትዮጵያ ጠንካራ የመከላከያ ኃይል፣ ትምህርት ቤቶች፣ መሰረተ-ልማቶችና ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን እንድታሳካ ግብር ከፋዮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል። 

በውጭና በውስጥ ችግሮች እየተፈተነች ቢሆንም በልማት ጉዞ ላይ መሆኗን ገልጸው፤ ለስኬታማነቱ ግብርን በታማኝነት መክፈል ያስፈልጋል ብለዋል። 

ኢትዮጵያ የሚያዋጣት ወንድማማችነት፣ አብሮ መኖር፣ ሕግን ማክበርና ጠንክሮ መሥራት መሆኑን ተናግረው ግብር ከፋዮች ለዚህ አርዓያ ሆነው እንዲገኙም ጠይቀዋል። 

በታማኝ ግብር ከፋዮች ጥረት የምታስቀና እና ጠንካራዋን ኢትዮጵያ እውን እናደርጋለን ሲሉም አረጋግጠዋል። 

በአድዋ የተገኘውን ድል ስናከብር በኢኮኖሚው መስክ የተጀመሩ ጥረቶችን በማሳካት ድህነትን ለማሸነፍ በጋራ ጥረት በማድረግ መሆን አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም