ቀጥታ፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከዓድዋ ድል የተረከበውን አንድነት፣ ጀግንነትና ጽናት ጠብቆ የኢትዮጵያ መከታ ሆኖ ይቀጥላል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 23/2015 የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከዓድዋ ድል የተረከበውን አንድነት፣ ጀግንነትና ጽናት ጠብቆ የኢትዮጵያ መከታ ሆኖ የሚቀጥል መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

የዓድዋ ድል 127ኛ ዓመት በዓል በመስቀል አደባባይ ድሉን በሚያስታውሱ የተለያዩ ዝግጅቶችና ወታደራዊ ትእይንቶች በድምቀት ተከብሯል፡፡

 የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን በጋራ ሆነው በፍፁም ጀግንነት አሸናፊ የሆኑበት ታሪካዊ እለት መሆኑን ገልጸዋል።

 በመሆኑም ከአድዋ የወረስነውን አንድነት፣ ጀግንነትና ጽናት በቀጣይነት ለአገራችን ክብርና ከፍታዋን ለማረጋገጥ በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።

 የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ በተሰማራባቸው አገሮች ሁሉ በተምሳሌት የሚነሳ አኩሪ ገደል የፈፀመ ጀግና ሰራዊት መሆኑን አስታውሰዋል። 

ኢትዮጵያ እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በብርቱ ልጆቿ እየገነባች መሆኑን ጠቅሰው ፤ ግድቡን በንቃት በመጠበቅ ከዓድዋ የወረስነውን ጀግንነት አስጠብቀን እናስቀጥላለን ብለዋል፡፡

 የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከዓድዋ ድል የተረከበውን አንድነት፣ ጀግንነትና ጽናት ጠብቆ የኢትዮጵያ መከታ ሆኖ የሚቀጥል መሆኑንም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ አረጋግጠዋል። 

የዘንድሮው የዓድዋ ድል በዓል በመከላከያ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ታሪኩን በሚመጥን መልኩ ከፍ ተደርጎ ስለመከበሩም ገልጸዋል፡፡

 የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ፤ የዓድዋ ድል አባቶቻችን ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩን የኩራታችን ምንጭ ነው ብለዋል፡፡ 

በዓሉ የመላ ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ቀን መሆኑን ጠቅሰው በመከላከያ ሰራዊት መሪነት ከፍ ባለ መልኩ እንዲከበር ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም