ቀጥታ፡

አባቶቻችን በአድዋ የተቀዳጁትን ድል በልማታችን አጠናክረን መቀጠል የእያንዳንዳችን ኢትዮጵያውን ግዴታ ነው -የአፋር ክልል መንግስት

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 23/2015 “አባቶቻችን በአድዋ የተቀዳጁትን ድል በልማታችን አጠናክረን መቀጠል የእያንዳንዳችን ኢትዮጵያውን ግዴታ ነው” ሲል የአፋር ክልል መንግስት አስታወቀ።

127ኛው የአድዋ ድል "አድዋ: አንድነት፣ ጀግንነትና ፅናት" በሚል መሪ ቃል በአፋር ክልል ሰመራ ዛሬ ተከብሯል።

በዓሉ የተከበረው በተለያዩ ትርኢቶች፣ ፓናል ውይይት እና መርሐግብሮች መሆኑን ከአፋር ክልል መንግስት የኮምዩኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በስ ነስዓቱ ላይ የአፋር ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የአገር መከላከያ ሰራዊት እና ፌደራል ፖሊስ አመራር እና አባላት፣ የአፋር ክልል የጸጥታ አካላት፣ነዋሪዎች እና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የብልጽግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢሴ አደም “የአድዋ ድል ጀግኖች አባቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው ውድ ሕይወታቸውን ገብረው ልጆቻቸው የነጻነት አየር እንዲተነፍሱ ያደረጉበት ታላቅ ታሪካዊ ክስተት ነው።” ብለዋል።

ከሁሉም ጫፍ የተጠራሩ ጀግኖች አርበኞች ለአገር ክብር እና ልዕልና ሲሉ ልዩነቶቻቸውን ውበታቸው በማድረግ አንድነታቸውን ከብረት አጠንክረው በጀግንነትና በጽናት እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የጠላት ጦር ድል መንሳታቸውን ገልጸዋል።

የአድዋ ድል ጀግኖች አርበኞች በአንድነትና በፅናት ጠላትን መክተው ወደ መጣበት በመመለስ ቅኝ ገዚዎችንና የቅኝ ገዥነት አመለካከትን ያንኮታኮተ፣ የመላው አፍሪካና በአጠቃላይ ለጥቁር ህዝቦችና ለተጨቆኑ የዓለማችን ክፍሎች አዲስ ምዕራፍ የከፈተ፤

የሰው ልጅ በተፈጥሮው ነጻና በማንም አምባገነን በቅኝ ግዛት ስር መሆን እንደሌለበት በተግባር ያሳየ፣ ለትግል ያነሳሳ በጥቁር ህዝቦች ላይ የነበረው የባርነት ቀንበር እንዲያከትም መሰረት ሆኗል በማለት ኃላፊ አቶ ኢሴ አደም ገልጸዋል።

ቀደምት አባቶቻችን ኢትዮጵያን ክብሯን አስጠብቀው፣ ዳር ድንበሯን አስከብረው ሉአላዊት ሀገር ከደምና ከአጥንት ዋጋ ከፍለው ለቀጣዩ ትውልድ አስረክበው ማለፋቸውን በማውሳት።

የዛሬው ትውልድም ከአባቶቹ የተረከበውን አደራ በአግባቡ አደራውን መወጣት ግድ ያሉት አቶ ኢሴ አባቶቻችን በ አድዋ የተቀዳጁትን ድል በልማታችን አጠናክረን መቀጠል የእያንዳንዳችን ኢትዮጵያውን “ የነፍስ ወከፍ ግዴታችን ነው” ብለዋል።

በአድዋ አስደማሚ ታሪክ የሰራችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ዛሬም በአገር መከላከያ ሰራዊት ታሪክ እየደገመች መሆኑን ተናግረዋል።

ሰራዊቱ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ከማስከበር አልፎም የጎረቤት ሀገራት ብሎም በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ሰላም እንዲሰፍን ቀዳሚ ተሰላፊ በመሆን በተሰማራባቸው ቀጠናዎች ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ረገድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ዓድዋን ስንዘክር፣ ስናስታውስ ከድሉ የምንቀስማቸውን በርካታ እሴቶችና ትምህርቶችን በየዘመኑ በመቀመር ኢትዮጵያችንን ወደ ተሻለ የብልጽግና ማማ ለማሸጋገር መሆን ይኖርበታል ነው ያሉት አቶ ኢሴ።

ብልጽግናችንን ለማሳካት የአድዋ ድል የአሸናፊነት ስነ ልቦና እና ፅናትን በመመርኮዝ በየተሰማራንበት የስራ ዘርፍ ሁሉ በታማኝነት፣ በቅንነት እና በሀገር ፍቅር ስሜት ማገልገል ይኖርብናል ብለዋል።

የልማት ውጥኖቻችን ግባቸውን መተው ዜጎች የተሻለ ኑሮ መኖር የሚችሉት “ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያ እኔ አለሁላት' በማለት ኢትዮጵያችን ከእያንዳንዳችን የምትጠብቀውን በመፈጸም ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች እና የተመቸች ኢትዮጵያን ማስረከብ እንደሚገባም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም