ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከማኑፋክቸሪንግ ባሻገር ቱሪስት የሚሳብበት ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

52
አዲስ አበባ መስከረም 27/2011 ''ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ብቻ የሚውሉ ሳይሆን ቱሪስት የምንስብበትና ሆቴሎችና መዝናኛዎችን የምናበረክትበት ነው" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የምረቃ ስነ-ስርአት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ መስፋፋት ለአገር ኢኮኖሚ መበልጸግና ለማህበራዊ እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። በአገሪቱ የሚገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለይ ለወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠራቸው ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚያደርጉም እሙን ነው። በዚህም ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ለቱሪስት መስህብነት ብሎም ሆቴሎችና መዝናኛዎችንም ለማበራከት የጎላ ሚና እንደሚኖራቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ለኢንዱስትሪ ልማት መስፋፋት ህብረተሰቡ በተለይ ደግሞ ወጣቶች በሙሉ አቅማቸውና ጉልበታቸው ከመንግስት ጎን በመሆን ለመስራት መነሳሳት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። የመጀመሪያው ምራፍ የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በ100 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን በ4 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባ  ነው፡፡ ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥርና በየዓመቱም ከ38 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንደሚያመነጭ ይጠበቃል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም