ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ውድድር ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ውድድር ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 23/2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ውድድር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።
በ16ኛ ሳምንት መርሐግብር ሀዲያ ሆሳዕና ከመቻል ከቀኑ 10 ሰአት እንዲሁም አርባ ምንጭ ከተማ ከወልቂጤ ከተማ ከምሽቱ 1 ሰአት ላይ በድሬዳዋ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በድሬዳዋ ስታዲየም 127ኛውን የአድዋ ድል በዓል አስመልክቶ በሄሊኮፍተር ስታዲየም ውስጥ የበዓል መልዕክት የያዙ ፍላየሮች እንደሚበተኑና የማርሽ ባንድ እና ሌሎችም ትርኢቶች እንደሚቀርብ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።
የስታዲየም በሮች ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ለተመልካች ክፍት እንደሚሆንና ተመልካቾች ጨዋታውን በነጻ መከታተል እንደሚችሉም ገልጿል።
የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ32 ነጥብ ይመራል።
ኢትዮጵያ መድን በ30 እንዲሁም ባህር ዳር ከተማ በ27 ነጥብ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ይዘዋል።
አርባ ምንጭ ከተማ፣ ኢትዮ ኤሌትሪክ እና ለገጣፎ ለገዳዲ ከ14ኛ እስከ 16ኛ ደረጃ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር ትናንት መጠናቀቁ ይታወቃል።