ቀጥታ፡

ከአድዋ ድል በመማር ለሀገር ብልፅግና መረባረብ ይኖርብናል - የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ

ድሬደዋ፤ የካቲት 23 ቀን 2015 (ኢዜአ) ፡- ከአድዋ የአንድነትና የትብብር ድል በመማር ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና መረባረብ ይኖርብናል ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ተናገሩ።

127ኛው የአድዋ ድል በዓል በድሬዳዋ ምድር ባቡር አደባባይ በወታደራዊ ትዕይንቶችና ሰልፎች እንዲሁም ለሰላምና ልማት መጠናከር በሚያበረታቱ ሌሎች ዝግጅቶች ዛሬ በድምቀት ተከብሯል።

ምክትል ከንቲባው በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ የአድዋ ገድል ቀደመት አባቶቻችንንና እናቶቻችን ለነፃነት በከፈሉት መሰዋዕትነት የተገኘ አኩሪ ድል ነው ብለዋል።

ድሉ ህያው የኩራት ምንጭ ነው ያሉት አቶ ሀርቢ ፤ የአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን ወኔ በመላበስ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና በመትጋት መረባረብ ይኖርብናል ሲሉ ገልጸዋል።

እንደ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ገለፃ፤ በተለይ ወጣቶች ለሀገር ሉአላዊነትና ከፍታ መረጋገጥ የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ አለባቸው።

በበዓሉ ላይ የተሳተፉት በኢፌድሪ አየር ኃይል የምስራቅ አየር ኃይል ሶስተኛ አየር ምድብ የሠራዊት ስነልቡና ግንባታ ኃላፊ ሻለቃ ጌታቸው ማሞ እንደተናገሩት፤"ሠራዊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ በዘመናዊ መሳሪያዎችና ቴክኖሎጂ ተደራጅቶ የሀገርን ሉአላዊነት በማስከበር የአድዋን ድል ለመድገም ምንግዜም ዝግጁ መሆኑን" ተናግረዋል ።

ለአድዋ ድል የተከፈለውን ሁሉንም መስዋዕትነት ለአዲሱ ትውልድ በማስተማር ኃላፊነታቸውን በመወጣት ትውልዱ ለሀገር ሰላምና ዕድገት እንዲተጋ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት አቶ ረመዳን አበበ ናቸው።

ወይዘሮ ሰሚራ ኢብራሂም በበኩላቸው፤ ከአድዋ ድል ወኔን በመላበስ ለሀገር የትኛውንም ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

የፌደራል ፖሊስ አባል ሳጅን አለማየሁ አጥናፉ ፤ ከአድዋ ድል የአባቶችን ፅናትና ወኔ በመውረስ የተጣለባቸውን ሀገራዊ ግዳጅ ለመወጣት ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም