የዓድዋ ድል በታሪካዊቷ ዓድዋ ከተማ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል በታሪካዊቷ ዓድዋ ከተማ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከበረ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 23/2015 የዓድዋ ድል በታሪካዊቷ ዓድዋ ከተማ የሶሎዳ ተራራ ግርጌ በተለያዩ መርሃ ግብሮች በድምቀት ተከበረ።
የ127ኛው የዓድዋ ድል በዓል በታሪካዊቷ ዓድዋ ከተማ ሲከበር በከተማዋና በዙሪያው የሚኖሩ ወገኖችና ሌሎችም ተገኝተዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኃይማኖት አባቶች፣ የፌደራል ፖሊስ አመራርና አባላት፣ የፌደራል መንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ወጣቶችና ሌሎች እንግዶች ተሳትፈዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የበአሉ ታዳሚዎች፤ የአብሮነትና የአንድነት እንዲሁም የአሸናፊነት መገለጫ የሆነውን ታላቅ በዓል በአገራዊ አንድነት ስሜት በማክበራቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የዓድዋ ድል በዓል ከኢትዮጵያም ባለፈ የመላ ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ምልክት በመሆኑ ክብሩን በጠበቀ መልኩ ለትውልድ ማስተላለፍ የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች "ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል፤ የዓለም የነፃነት ተምሳሌት፤ የጥቁር ህዝቦች የድልና ኩራት" መሆኑን የሚገልጹ መፈክሮችን በመያዝ ጭምር አክብረውታል።
የዘንድሮው 127ኛ የዓድዋ ድል በዓል "አንድነት፣ ጀግንነትና ጽናት" በሚል መሪ ሃሳብ በመላ አገሪቷ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ውሏል።
በአዲስ አበባም በወታደራዊ ትርኢቶች ታጅቦ የበዓሉን ታላቅነት በሚያሳይ መልኩ በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት በመስቀል አደባባይ ተከብሯል።