የአድዋ ድል የተገኘው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአንድነትና በትብብር ባደረጉት ተጋድሎ ነው-የጋምቤላ ክልል መንግስት - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል የተገኘው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአንድነትና በትብብር ባደረጉት ተጋድሎ ነው-የጋምቤላ ክልል መንግስት
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 23/2015 “የአድዋ ድል የተገኘው የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአንድነትና በትብብር ባደረጉት ተጋድሎ ነው” ሲሉ የጋምቤላ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ቸንኮት ቾት ገለጹ።
‘‘አድዋ አንድነት፣ ጀግንነትና ጽናት’’ በሚል መሪ ሃሳብ 127ኛው የአድዋ ድል በዓል በጋምቤላ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ ወታደራዊ፣ ባህላዊ ትርኢትና ሌሎች የኪነ ጥበብ ሌሎች ክንዋኔዎች ቀርበዋል።
የጋምቤላ ክልል ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ቸንኮት ቾት እንዳሉት፤ “ጀግኖች አባቶች የአድዋ ድል ታሪክ የተጎናጸፉት በዘር፣ በቀለም፣ በቋንቋና በሃይማኖት ሳይለያዩ በአንድነት በመታገል ነው፤ ድሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ትብብር ውጤት ነው።”
የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ሕዝቦች ብሔራዊ ክብር፤ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተጋድሎ አርማ መሆኑን ገልጸዋል።
ድሉ የጣሊያን ወራሪ ብቻ ሳይሆን የቅኝ ግዛት ፍላጎትና ምኞት የነበራቸውን የነጮች ቅስም በመስበር ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው የአፍሪካ ሕዝብ ያኮራ ታላቅ ታሪካዊ ክስተት እንደሆነም ተናግረዋል።
በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ የጀግኖች አባቶችን የአንድነትና የአብሮነት እሴቱን በማጽናት ድህነትን ጨምሮ ሌሎች ፈተናዎችን በድል ለመሻገር በጋራ መረባረብ እንዳለበት ነው አቶ ቸንኮት ያሳሰቡት።
ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ገናና ታሪኮች መካከል የአድዋ የድል ታሪክ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጋምቤላ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኡቡላ ኡቦንግ ናቸው።
ይህን የአባቶቻችን ታሪክ አስጠብቆ ለትውልዱ ለማስተላለፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በአድዋ ድል በዓል አከባበር ላይ የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።