ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ትግል ተምሳሌት፤ የሉዓላዊነታችን ማህተም ነው - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ትግል ተምሳሌት፤ የሉዓላዊነታችን ማህተም ነው - የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
አዲስ አበባ የካቲት 23/2015(ኢዜአ)፦ዓድዋ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ትግል ተምሳሌት፤ የሉዓላዊነታችን ማህተም ነው ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ።
አገልግሎቱ የ127ኛው የዓድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ ለመላ ኢትዮጵያውያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦የካቲት 23/1888 ዓ.ም አባቶቻችን የተጎናፀፉት የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ነፃነታቸውንና ሉዓላዊነታቸውን ሊገፍ የመጣውን የሰለጠነ ወራሪ ጦር በታላቅ በጀግንነት ወኔ፣ በአንድነትና በጽናት ያሸነፉትበት እለት ነው።
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በአንድ የፍቅር ገመድ ያሰናሰለ የነፃነት እና ሉዓላዊነት ብስራት ነዉ። ድሉ የኢትዮጵያ ሕብረብሔራዊ አንድነት የጸናበት የማዕዘን ድንጋይም ነው፡፡
የዓድዋ ድል ለጊዜያዊ ውጤቱ ባሻገር የዓለም የሰው ልጆችን ታሪክ ጭምር የቀየረ በደማቅ ቀለም የተፃፈ ድል ነው፡፡ድሉ ከማሸነፍም ባሻገር የኢትዮጵያዊ አንድነት የፀናበትና የመተባበራችን ዉጤት ማሳያ መስታወት ሆኖ ሲዘከር ቆይቷል፡ ፡
የኢትዮጵያ ልጆች ለአንድ የጋራ ሀገራቸው ከአራቱም አቅጣጫ በአንድ ጥሪ ተሰባስበው፤ የጋራ ጠላትን ድል በመንሳት ሕልውናቸውን ያረጋገጡት አንዱ እና ዋነኛዉ በዓድዋ ድል ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያን የጋራ ጥቅማቸው የሚከበረው በመተባበር እንጂ በመለያየት እንዳልኾነም የዓድዋ ድል ኽያዉ ምስክር ነው፡፡
ኢትዮጵያዊያን ለአንድ ዓላማ፤ በአንድነት አብረው በጋራ ሲሰለፉ ምን አይነት ውጤት እንደሚያመጡ በዓድዋ ድል ተረጋግጧል፡፡ የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ነፃነትን ያበሰረ ነበር።
የአድዋ ድል ለፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤ መፀነስ ትልቅ መሠረት የጣለ ክስተትም ሆኗል፡፡ በዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች የነበራቸው የአመራር ብቃት፣ ዕናት፣ ጀግንነትና የዓላማ አንድነት ምንግዜም የሚታወስ ነዉ፡ በወቅቱ ኢትዮጵያዊያን በውስጣቸው የነበረዉን ልዩነት ወደ ጎን በመተዉ የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበርና ለማዕናት በጋራ መቆማቸዉ የዓድዋን ድል እንድንጎናፀፍ አድርጎናል፡፡
የዓድዋ ድል መንፈስ በቀጣይ ተከታታይ ትውልዶች አዕምሮ ውስጥ የተቀረፀ የድል ሐውልት በመኾኑ፤ ኢትዮጵያ የሚያጋጥሟትን ሀገራዊ ፈተናዎች በጋራ ርብርብ መፍታት እደምትችል ቁምነገር ያስጨበጠ ነው፡፡
የዛሬው ትውልድ በአድዋ ድል የታየውን የአባቶቹን ጀግንነት፤ አንድነት እና የዓላማ ፅናት በተለያዩ መስኮች መድገም ይኖርበታል፡፡ በዘመናችንም በሕዳሴው ግድብ ግንባታ፤ የአሸባሪዎችን ጥቃት በመመከት፤ በአረንጓዴ አሻራ፤ እና በሌሎችም መስኮች የታየው ሕብረትና ያመጣው ውጤት፤ በዓድዋ ድል መንፈስ መንቀሳቀስ ውጤቱ አጥጋቢ እንደሚኾን የሚያስገነዝብ ነው፡፡
የዛሬዉ ትዉልድ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመቆም የሀገራችንን የብልፅግና ጉዞ ከግቡ ማድረስ እንደምንችል ከዓድዋ ድል ትምህርት መዉሰድና በተሰማራንበት መስክ ሁሉ የአባቶቻችንን የአሸናፊነት መንፈስ በመሰነቅ ለአገራችን የሚጠበቅብንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል።
ለመላዉ ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለ127ኛዉ የዓድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ!! ዓድዋ፡ አንድነት፣ ጀግንነት እና ጽናት!!
የካቲት 23/2015 ዓ/ም
አዲስ አበባ በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት