ቀጥታ፡

127ኛው የዓድዋ ድል በዓል ታላቅነቱን በጠበቀ መልኩ በመከበሩ ክብርና ኩራት ተሰምቶናል-ልጅ ዳንኤል ጆቴ

አዲስ አበባ የካቲት 23/2015 (ኢዜአ) 127ኛው የዓድዋ ድል በዓል ታላቅነቱን በጠበቀ መልኩ በመከበሩ ክብርና ኩራት ተሰምቶናል ሲሉ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ተናገሩ።

127ኛው የዓድዋ ድል በዓል በመስቀል አደባባይ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ ለጥቁር ሕዝቦች የይቻላል መንፈስን ያበሰረችበት ድል ነው ብለዋል፡፡

በዓድዋ ጦርነት ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ነጻ አገር ያስረከቡን ጀግኖች ዘወትር ሊመሰገኑ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የመከላከያ ሠራዊት እንደ ቀደምት የዓድዋ ጀግኖች ሁሉ የአገሩን ሉዓላዊነትና ህልውና ለመጠበቅ እያከናወነ ያለው ተግባር የሚያኮራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዓድዋ ድል በዓል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝቦች መመኪያ በመሆኑ መንግሥት በመከላከያ ሠራዊት መሪነት እንዲከበር በማድረጉ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል።

በተለይ በዓሉ በደመቀ መልኩ እንዲከበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከፍተኛ የመከላከያ መኮንኖች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም