የዓድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን የአንድነት መገለጫ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ምልክት ነው - የዓድዋ ከተማ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 23/2015 የዓድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን የአንድነት መገለጫ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ምልክት መሆኑን የዓድዋ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ነዋሪዎቹ 127ኛው የአድዋ ድል በዓል በሰላም ስምምነቱ ማግስት መከበሩ ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

 አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች የዓድዋ ድል በዓል ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ዘምተው ጠላትን ድባቅ የመቱበት የድል አሻራ መሆኑን አንስተዋል። 

ድሉ ከኢትዮጵያውያን አልፎ ለመላው ጥቁር ህዝብ የይቻላል መንፈስን ያጎናጸፈ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሆነው በአድዋ ያስመዘገቡትን አኩሪ የድል ታሪክ በአርአያነት በመውሰድ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ እንደሚተጉ ተናግረዋል።

 "አባቶች በታላቅ ታሪካዊ ገድል ጠብቀው ያስረከቡንን አገር እኛም ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን" ብለዋል ነዋሪዎቹ።

 በፌዴራል መንግስትና በህወሃት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አጽንቶ ለማስቀጠል የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

 የዓድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን የአንድነት መገለጫ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ምልክት መሆኑን በመጥቀስ በአንድነት ሰላምን ማጽናት ይገባል ብለዋል።  

ከሰላም ስምምነቱ ወዲህም የዓድዋ ከተማ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደረገች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

 የፌደራል መንግሥት ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ነዋሪዎቹ አድንቀዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም