ቀጥታ፡

ቦርዱ በደቡብ ክልል የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ ውጤት ይፋ አደረገ

የካቲት 22/2015  (ኢዜአ)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ ውጤት ይፋ አደረገ።

የወላይታ ዞን ህዝበ ውሳኔ ምርጫ በድጋሚ እንዲካሄድ መወሰኑንም አስታውቋል።

ቦርዱ በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ ውጤት አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።  

በክልሉ ወላይታ ፣ጋሞ፣ጌዲኦ ፣ጎፋ ፣ኮንሶና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ህዝበ ውሳኔ መካሄዱ ይታወሳል፡፡

 ቡርጂ ፣ባስኬቶ፣አሌ፣አማሮ እና ዲራሼ ልዩ ወረዳዎችም በተመሳሳይ ድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

 የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብእሸት አየለ የህዝበ ውሳኔ ውጤቱ እና አጠቃላይ ሂደቱን ለመገናኛ ብዙሃን በንባብ ይፋ አድርገዋል።

 ቦርዱ ምርጫውን ለማካሄድ ሰፊ ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ወደ ስራ መግባቱን አስታውሰው፤ በጋራ ክልል መመስረት እንፈልጋለን የሚሉ "ነጭ እርግብ" ምልክትን በነባሩ ክልል እንቀጥላለን ያሉት ደግሞ "የጎጆ ቤት" ምልክትን መርጠዋል ነው ያሉት።

 በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ምርጫ የወላይታ ዞንና በሌሎች ዞንና ልዩ ወረዳዎች ውጤታቸው ያልተካተተ 81 ጣቢያዎችን ሳይጨምር የህዝበ ውሳኔ ውጤቱን ይፋ አድርገዋል።

 በዚሁ መሰረት በኮንሶ 101,114 መራጮች በአዲስ ክልልነት ለመደራጀት ድምጽ ሲሰጡ 1,890 ደግሞ በነባሩ ክልል እንቀጥል በሚል ድምጽ ሰጥተዋል ብለዋል።

 በደቡብ ኦሞ ዞን 256 ሺህ 159 መራጮች በአዲስ ክልነት ለመደራጀት የቀረበውን አማራጭ ሲመረጡ 5 ሺህ 364 ድምጽ ሰጪዎች ደግሞ በነባሩ ክልል ለመቀጠል ድምጽ መስጠታቸውን አንስተዋል።  

በተመሳሳይ በጋሞ ዞን 583 ሺህ 757 መራጮች በአዲስ ክልልነት እንደራጅ የሚል ድምጽ ሲሰጡ 9 ሺህ 682 በነበሩ ክልል ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው በሰጡት ድምጽ ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።

  እንደ ምክትል ሰብሳቢው ገለጻ፤ በጌዲኦ ዞንም 241 ሺህ 695 መራጮች በአዲስ ክልል መደራጀትን ሲመርጡ 46 ሺህ 749 መራጮችች ደግሞ በደቡብ ክልል ስር ለመቀጠል ድምጽ ሰጥተዋል፡፡

 በጎፋ ዞንም 243 ሺ 327 መራጮች በአዲስ መልክ ክልል ለመሆን ሲወስኑ 12 ሺህ 306 በነባሩ ክልል ለመቀጠል ድምጽ መስጠታቸውን ይፋ አድርገዋል።  

በክልሉ ባሉት አምስት ልዩ ወረዳዎች የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ ውጤትም ገልፀዋል ምክትል ሰብሳቢው እንዳሉት፤ በወላይታ ዞን የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ከምርጫው ህግ ጥሰት ጋር በተያያዘ በድጋሚ እንዲካሄድ መወሰኑን ተናግረዋል።

  በወላይታ ዞን እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ዜጎች ድምጽ መስጠታቸው፣ሌላ ሰው መምረጥ፣ምርጫ ምስጢራዊነትን መጣስ፣የታዛቢነት ባጅ ሳይኖራቸው በምርጫ ጣቢያ ታዛቢነት መገኘት እና የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን ማጨቅ በምርጫ ሂደቱ ከተገኙ ግድፈቶች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

 በዞኑ ጥሰቶች በተፈጸሙባቸው ምርጫ ጣቢያዎች ጥሰቶችን ያስፈጸሙ፣የፈጸሙና የተባበሩ አካላትን በመለየት ምርመራ እንዲካሄድ ጉዳዩ ወደ ፌደራል ፖሊስ እንዲመራ ቦርዱ መወሰኑን አብራርተዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ እንደተናገሩት፤በወላይታ ዞን የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ምርጫ ውጤት የተሰረዘው በርካታ ተአማኒነት የጎደላቸው ድርጊቶች በመገኘታቸው ነው ብለዋል።  

በመሆኑም ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ መወሰኑን አስታውቀዋል።

 በቀጣይ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች እንዳይገጥሙ ከምርጫ አስፈጻሚ ጀምሮ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ትምህርት የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።  

      

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም