የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የአንድነት መገለጫ፣ የአሸናፊነትና የሉዓላዊነት ማረጋገጫ ነው--ዶክተር ይልቃል ከፋለ - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የአንድነት መገለጫ፣ የአሸናፊነትና የሉዓላዊነት ማረጋገጫ ነው--ዶክተር ይልቃል ከፋለ

አዲስ አበባ የካቲት 22/2015(ኢዜአ)፦ የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የአንድነት መገለጫ፣ የአሸናፊነትና የሉዓላዊነት ማረጋገጫ ነው ሲሉ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ-መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።
ርዕሰ-መስተዳደሩ 127ኛውን የአድዋ የድል በዓል አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያ ብሔራዊ ክብርና ኩራት ብቻ ሳይሆን የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት ጭምር ነው ብለዋል።
አድዋ ድል የነጻነትና የአገር ሉአላዊነት መሐዲስና አርበኛ በሆኑት አጼ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ በሰጡት ወታደራዊ የአመራር ጥበብ መላ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት በመሆኑ ኢትዮጵያ በነጻነቷ ጸንታ እንድትዘልቅ አስችሏታልም ብለዋል።
ድሉ አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ አዲስ የጥቁር ህዝቦች ነጻነት ታሪክ የተመዘገበበት እንጂ ወታደራዊ ድል ብቻ አይደለም ብለዋል።
ጀግኖች አባቶቻችን የጠላት ኃይል ሚዛን ሳይበግራቸው ጦርና ጎራዴ አንግበው በተባበረ ብርቱ ክንድና መስዋዕትነት ጠላትን አንበርክከው ጀግንነትና አርበኝነትን፣ ክብርና ነጻነትን አውርሰዋል፤ የአገራቸውን ሉአላዊነት በጽኑ መሠረት ላይ አኑረዋል፤ አንጸዋል፤ ለአገራቸው ክብርን አጎናጽፈዋል ብለዋል።
በአንድነት፣ በፍትህና በእውነት የጸና ሕዝብ ሁሌም አሸናፊና ባለድል እንደሚሆን አያጠራጥርም፤ የአሸናፊነትና ድል አድራጊነታቸው ምክንያት ደግሞ ሀገራዊ ፍቅርና የስነልቦና አንድነት ነው በማለት አስረድተዋል።
ነጻነትና ክብር ያለ መስዕዋትነት፣ ድልና ጀግንነት ያለ ተጋድሎ መጎናፈጸፍ አይታሰቡም ያሉት ርዕሰ-መስተዳድሩ አድዋ የኢትዮጵያውያን የአርበኝነት አርማ፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ አሻራና ሰብአዊ ክብር የተረጋገጠበት ታላቅ ድል ነው ብለዋል፡፡
ከአድዋ ድልም የምንማረው እብሪተኝነትና ግፈኝነት ከሽፎ እውነትና ፍትሕ አሸናፊ የሆኑበት ክስተት መሆኑን ነው ብለዋል።
ስለሆነም የአድዋ ድል 127ኛ ዓመት ስንዘክር ልዩነቶቻችንን ሁሉ ወደ ጎን ትተን ህብረትን፣ መተባበርንና አገራዊ አንድነትን መርህ ማድረግ ይኖርብናል በማለት ለመላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ለ127ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ ቀን በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል።