በአድዋ ጦርነት የተገኘውን ድል በዲፕሎማሲ በመድገም ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ማውጣት እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በአድዋ ጦርነት የተገኘውን ድል በዲፕሎማሲ በመድገም ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ማውጣት እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 22/2015 በአድዋ ጦርነት የተገኘውን ድል በዲፕሎማሲው መስክ በመድገም ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ለማውጣት ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
ኢዜአ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎትና የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩትን ሃላፊዎች ነገ የሚከበረውን የአድዋ ድል በዓልን አስመልክቶ አነጋግሯቸዋል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአድዋ ድል ጥቁሮች ከነጮች እኩል መሆናቸውን ያሳየ ነው፡፡
ራሳቸውን ቀዳማይ ማንነት ያላቸውና የዓለም መሪ አድርገው የሾሙ አውሮፓውያን መሪዎች አፍሪካን ለመቀራመት ያቀዱትን ህልም ከንቱ ያስቀረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአድዋ ድል የጥቁር ህዝቦችን አንገት ቀና ያደረገ፤ የቅኝ ገዥዎችን ህልም ያመከነ የጭቆና ቀንበርን የሰበረ የመላው ጭቁን ህዝቦች ኩራት ነውም ብለዋል፡፡
የሰው ልጆችን እኩልነት በተግባር ያረጋገጠ ከኢትዮጵያ የፈነጠቀ ድል መሆኑን ገልፀው የቀኝ ገዢዎች እሳቤ የተመታበት መድረክ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የጥናትና ምርምር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ የዐድዋ ጀግኖች ለሀገራቸው ክብር፣ ለህዝባቸውና ባንዲራቸው ከፍታ ሲሉ ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው በጋራ ቆመው ጠላትን ድል አድርገዋል ብለዋል፡፡
አድዋ አፍሪካ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ በወደቀችበት ዘመን ኢትዮጵያ በጀግኖች አርበኞቿ ተጋድሎ ነጻነት እና ሉዓላዊነቷን ያስጠበቀችበት ድል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የአድዋ ድል ኢትዮጵያ በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ለአፍሪካውያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ እንዲሰጥ ለምታደርገው ጥረት ፈር ቀዳጅ ምሳሌ ይሆናልም ብለዋል፡፡
ተቋማቱ በዐድዋ ጦርነት የተገኘውን ድል በዲፕሎማሲው መስክ በመድገም ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ለማውጣት ጠንክሮ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡