ቀጥታ፡

በአድዋ መንፈስ ሆነን በድሉ ብስራት ጠንክረን፤ ኢትዮጵያ የምትጠብቅብንን ደማቅ ታሪክ ዳግም መስራት መቻል አለብን - ከንቲባ አዳነች አቤቤ


አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 22/2015 “በአድዋ መንፈስ ሆነን በድሉ ብስራት ጠንክረን፤ ኢትዮጵያ የምትጠብቅብንን ደማቅ ታሪክ ዳግም መስራት መቻል ይገባናል” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

“ልክ አድዋ ላይ ጀግኖች እንዳደረጉት ትልቁን መዳረሻችንን በማለም አብረን መቆም ይኖርብናልዕ" ብለዋል።

ከንቲባ አዳናች አቤቤ ነገ ለሚከበረው 127ተኛው የአድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

“አድዋ የጀግንነት፣ የአብሮነት፣የጽናት፣ የአንድነት፤ መዝገብ ነው፤ በአድዋ ላይ በክብር ያልወደቀ ኢትዮጵያዊ፤ለድል አድራጊነት ያልታገለ ኢትዮጵያዊ የለም” ሲሉም ተናግረዋል።

“በአድዋ ጦርነት እንስሳት ተዋግተዋል፤ ተራሮች ተፋልመዋል፤ የአድዋ ድል የሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ ዘላለማዊ ድል የሆነው በአፈጻጸም ብቃት የጠነከረ፣ በተሳትፎ ስፋት የተዋቀረ፣ በዓላማ ጽናት የተቀመረ፤ መሆኑ ነው“ ብለዋል በመልዕክታቸው።

አድዋ የግል ክብርንና ኩርፊያን በእውነተኛ የኢትዮጵያ ፍቅር እንዲተካ ያደረገ ደማቅ ድል በመሆኑ ‘አኩርቶናል አስተሳስሮናል አዋህዶናል” ነው ያሉት።

ከአድዋ ጀግኖች አሸናፊነታቸውን ብቻም ሳይሆን ለማሸነፍ ያበቋቸውን ጉዳዮች ከመረመርን ለዛሬ ማንነታችን የተሰነቁ እኛም አጉልተን ልንጠቀምባቸው የሚገቡ ትምህርቶች እንዳሉ ተናግረዋል።

“አድዋን ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ፤ ከዛም ተሻግሮ ለመላ ጥቁር ህዝቦች የነጻነት እስትንፋስ እንዲሆን ያበቃው አንድነትን ከጀግንነት ፣ ዓላማን ከጽናት፤ አስተባብሮ የያዘ ምልክት በመሆኑም ጭምር ነው” ብለዋል፡፡

“ዛሬም በአድዋ መንፈስ በመሆን፤ በድሉ ብስራት በመጠንከር ኢትዮጵያ የምትጠብቅብንን ደማቅ ታሪክ ዳግም መስራት መቻል ይገባል” ያሉት ከንቲባዋ “ብዙ ያልሰራነው ፣ ገና ያልፈጸምነው፤ ስራ አለብን” ሲሉ ተናገረዋል።

“አየሩን በሚሞሉት አሉታዊ እሳቤዎች ወደ ኋላ እየተጓተትን የአድዋን ፍሬ መብላት አንችልም” ፤ ልክ አድዋ ጀግኖች እንዳደረጉት ትልቁን መዳረሻችንን አልመን ለማስተካከል አብረን መቆም ይኖርብናል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም