የአድዋ ድል የማይደበዝዝና የማይነጥፍ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ጥሪታችን ነው- ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል የማይደበዝዝና የማይነጥፍ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ጥሪታችን ነው- ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ
አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 22/2015 “የአድዋ ድል ቀደምት ጀግኖች አያቶቻችን ያበረከቱልን ዘውትር የማይደበዝዝና የማይነጥፍ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ጥሪታችን ነው” ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገለጹ።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ነገ የሚከበረውን 127ኛው የአድዋ ድል በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
“የአድዋ ድል በዓል በዓለም ደረጃ ለዘመናት ከፍ እንድንል ኢትዮጵያዊያን በላባቸው: በደማቸውና በአጥንታቸው ያፀኑት ዘመን የማይሽረው ኩራታችን: ክብራችንና የነጻነታችን አርማ ነው” ብለዋል ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ።
“አድዋ የሕብረ ብሄራዊነት መገለጫ የአንድነትና አይበገሬነት ተምሳሌት፤ቀደምት ጀግኖች አያቶቻችን ያበረከቱልን ዘውትር የማይደበዝዝና የማይነጥፍ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ጥሪታችን ነው” ብለዋል።
በዓሉ የቅኝ ግዛት ዘመን ትርክትን የቀየረ ኢትዮጵያዊ ገድል መሆኑንም አመልክተዋል።
የአድዋ ጦርነት ድል ለጣሊያኖች ሽንፈት አስከትሎ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማጽናት ባሻገር ከአድማስ ተሻግሮ አህጉራትን አቋርጦ የተሰማ ጉልህ ተጽዕኖን በዓለም ዙሪያ ማስከተሉን ተናግረዋል።
ድሉ በዘመናዊው ዓለም የፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ውስጥ የኢትዮጵያ ስም ተደጋግሞ ከሚነሳባቸው ክስተቶች መካከል አንዱ ለመሆን ከመብቃቱ ባሻገር ጥቁሮች ለነጻነት በሚያደርጉት ትግል ውስጥ መነቃቃትንና ተስፋን የሰጠ ክስተት ሆኗል ብለዋል ።
“የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማህተም፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው” ሲሉ የተናገሩት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዓሉን ስናከብር በክልሉ የተጀመሩ ልማታዊ ስራዎች ተጠናክሮ እንዲቀጥል መስራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በልማት ስራውም በመድገም የኢትዮጵያን ብልፅግናን ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ መትጋት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
በአድዋ አባቶች የተገኘው አንድነት፣ጀግንነት እና ጽናትም በዚህ ዘመን ትውልድ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።