አንድነትን በማጽናት ፈተናዎችን ለመሻገር በጋራ መስራት ይገባል-የሰላም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
አንድነትን በማጽናት ፈተናዎችን ለመሻገር በጋራ መስራት ይገባል-የሰላም ሚኒስቴር
አዲስ አበባ (ኢዜአ)የካቲት 22/2015 እንደ አድዋ ድል አንድነትን በማጽናት ፈተናዎችን ለመሻገር በጋራ መሥራት ይገባል ሲሉ የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ገለጹ።
የሰላም ሚኒስቴር፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት፣ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አመራርና ሰራተኞችን 127ኛውን የአድዋን ድል በዓል ዛሬ በጋራ አክብረዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ ታዬ ደንደአ እንደገለጹት፤ ጀግኖች የአድዋ አባቶች ያስረከቡንን አገር ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ በጋራ መሥራት አለብን።
በአድዋ የተገኘው ድል አንድነትን በማጽናት ቀጣይ ፈተናዎችን ለመሻገር ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥራል ነው ያሉት።
ድሉ ከኢትዮጵያ አልፎ የመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ገድል ነፀብራቅ በመሆኑ የአሁኑ ትውልድ ከአድዋ ተምሮ አገሩ በልማትና በዴሞክራሲ ግንባታ ማሻገር ይጠበቅበታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በከባድ ፈተና ውስጥ ሆና ጀግንነትን በማሳየት በጽናት እና በአንድነት ያለች ሀገር መሆኗንም ገልጸው ትውልዱ ይህንን ሊያስቀጥል ይገባል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰሎሞን ሶካ በበኩላቸው፤ የአድዋ ድል ከኢትዮጵያውያን ድል ባለፈ የጥቁር ህዝቦችም ሁሉ ድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአድዋ ድል በአንድነት፣ በፅናት፣ በህዝባዊ ተጋድሎና መስዋዕትነት የተመዘገበ ታሪካዊ ድል መሆኑን ጠቅሰው፤ በጦርነቱ ከተሳተፉ ጀግኖች አባቶችም የአሁኑ ትውልድ ሊማር ይገባል ብለዋል።
የማህበራዊ አንድነትን በመሸርሸር ሕዝብን ከሕዝብ እያጋጩ ለመከፋፈል የሚሞክሩ ከፋፋዮች በጋራ መመከት ይገባልም ነው ያሉት።
በመርሃ ግብሩ የሰላም ሚኒስቴር ፤የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት፣ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ አመራርና ሰራተኞችን ጨምሮ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።