ቀጥታ፡

የቀደሙ አባቶች በአድዋ በሕብረት ያስመዘገቡትን ድል ወጣቱ በልማት ሊደግመው ይገባል - የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር

የካቲት 22 ቀን 2015 (ኢዜአ) "የቀደሙ አባቶች በአድዋ በሕብረት ያስመዘገቡትን ድል ወጣቶች አንድነታችንን በመጠበቅ በልማት ልንደግመው ይገባል" ሲል የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ብሎም የጥቁር ሕዝቦች የአሸናፊነት ምልክት የሆነው የአድዋ ድል መንስኤው የውጫሌ ስምምነት አንቀፅ 17 የአማርኛና ጣሊያንኛ ትርጉም መፋለስ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል፡፡

"ኢትዮጵያ ስትፈልግ የውጭ ግንኙነቷን በጣሊያን መንግሥት በኩል ማድረግ ትችላለች" የሚለው የአማርኛ ቅጂ እና "ኢትዮጵያ ማንኛውንም የውጭ ግንኙነት በጣሊያን በኩል ታደርጋለች" የሚለው የይዘት ተቃርኖ እንደሆነም ይነገራል፡፡

የጣሊያን መንግሥት የጣሊያንኛ ትርጉሙን በግድ ለማስፈጸም ያደረጉት ሙከራ ያስቆጣቸው ዳግማዊ አፄ ምንሊክ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ሉዓላዊነት እንዲዘምቱ የክተት ጥሪ ማስተላለፋቸውም ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያውያን ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት፣ ፆታ ሳይለያቸው በአንድነት በመዝመት የካቲት 1888 ዓ.ም የጣሊያንን ወራሪ ኃይል ድባቅ በመምታት አይበገሬ መሆናቸውን ለዓለም አሳይተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ዋና ጸሐፊ ይሁነኝ መሐመድ ለኢዜአ እንዳለው፤ የአድዋ ድል ለውጭ ኃይል ተገዠ ያለመሆንን፣ በራስ መቆምና በማንነት መኩራትን አስተምሮናል፡፡

ጀግኖች አያቶቻችን ለመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች ኩራት በዘመናት ብዛት የማይደበዝዝ ጀብዱ በደማቅ ቀለም እንደጻፉት ሁሉ እኛም ኢትዮጵያን በልማት ከፍ በማድረግ አድዋን መድገም ይገባናል ብሏል፡፡

ድሉ በዘመኑ ወጣቶች ልበ-ሙሉነት፣ ብርታትና የተባበረ ክንድ "ከእኔ በላይ ለሀገሬ" በሚል ኢትዮጵያዊ ወኔና መንፈስ የተመዘገበ በመሆኑ ብዙ የሚማሩበትና የሚሰሩበት መሆኑን ነው ዋና ጸሐፊው የገለጸው፡፡

ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘናት በመትመም ሀገራቸውን የድል ካባ እንዳለበሷት ሁሉ የእኛ ትውልድ ደግሞ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም በመገንባት ኃያልነቷን ማሳየት አለበት ብሏል፡፡

የዚህ ዘመን ፈተና የሆነውን ግለኝነት እና ጽንፈኝነት በመታገል በተባበረ ክንድ በልማት ኢትዮጵያን ከድህነት ማውጣት የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነት መሆኑን አመልክቷል።

በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሽግግር ማምጣት የሚጠይቅበት ወቅት መሆኑን የገለጸው ወጣቱ፤ ልዩነቶችን በሰከነ መንፈስ በውይይት በመፍታት ከዘመናዊ የኢኮኖሚ ባርነት መውጣት እንደሚገባም ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም