ቀጥታ፡

የአድዋ ድል ኢትዮጵያን በትብብር ወደ ተሻለ ከፍታ መውሰድ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ነው-ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ

አዲስ አበባ(ኢዜአ)የካቲት22/2015 "የአድዋ ድል ኢትዮጵያን በትብብር ወደ ተሻለ ከፍታ መውሰድ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አመራሮች እና አባላት 127ኛውን የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በፓናል ውይይት አክብረዋል።

በመርሃ-ግብሩም የአድዋ ድል ታሪካዊ ዳራን የሚያሳይ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ በዚሁ ወቅት "የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን የመተባበር ውጤት፤ የጀግንነት ምሳሌ ነው" ብለዋል፡፡

በመሆኑም በዓሉ ይህን በሚመጥን መልኩ በድምቀት ይከበራል ነው ያሉት፡፡

የአድዋ ድል ኢትዮጵያን በትብብር ወደ ተሻለ ከፍታ መውሰድ እንደሚቻል ትምህርት እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የአድዋ ድልን ስናከብር በቀጣይ አገራችንን ወደ ብልጽግና ጎዳና ለመውሰድ የሞራል ስንቅ አድርገን በመውሰድ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መመርያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ነብዩ ዳኜ በበኩላቸው የአድዋ ጦርነት ከኢትዮጵያ ባሻገር የቅኝ ግዛት እሳቤን የታገለ የአፍሪካዊያን ድል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በዚህም ድሉ የሰው ልጆች ሁሉ እኩል መሆናቸውን በተግባር ያሳየ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም የተሻለች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ በማሸጋገር የአድዋ ጀግኖች አደራን መወጣት አለብን ነው ያሉት፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የፌደራል ፖሊስ አባላት በበኩላቸው የአድዋ ድል ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ አገርን በጋራ የማጽናት ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ትውልዱ አንድነቱን በማጠናከር አገሩን በጋራ መጠበቅ እንዳለበት ነው የገለጹት፡፡

ለዚህ ደግሞ እንደ አድዋ ድል ጀግኖች አንድነትና ትብብራችንን በማጠናከር ለኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ ለመስራት በጋራ መቆም አለብን ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም