"አድዋ የመላው ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት የነጻነት ድል ነው"- ገጣሚና ጸሃፈ-ተውኔት አያልነህ ሙላቱ - ኢዜአ አማርኛ
"አድዋ የመላው ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት የነጻነት ድል ነው"- ገጣሚና ጸሃፈ-ተውኔት አያልነህ ሙላቱ
አዲስ አበባ (ኢዜአ)የካቲት 22/2015 "አድዋ የመላው ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት የነጻነት ድል ነው" ሲል ገጣሚና ጸሃፈ-ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ተናገረ፡፡
ነገ 127ኛውን የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በአገር አቀፍ ደረጃ በታላቅ ድምቀት ይከበራል።
በዓሉን በተመለከተ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከገጣሚና ጸሃፊ-ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ጸሃፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ በዚሁ ወቅት "አድዋ እንደሰንሰለት የተያያዘ የድል ሽግግር እንጂ አንድ ቦታ ብቻ በአንድ ጊዜ የተፈጸመ አይደለም" ብሏል፡፡
ከአድዋ ጦርነት በኋላ በማይጨው፣ በካራማራና በሌሎች የጦር ሜዳዎች በተካሔዱ ጦርነቶች የተገኙ ውጤቶች የአድዋ ጦርነት ትሩፋቶች መሆናቸውን ገልጿል፡፡
በጦርነቱ መላው ኢትዮጵያውያን የዘር፣ የቀለም፣ የሃይማኖትና የፖለቲካ ልዩነት ሳይበግራቸው ከየአቅጣጫው በመሰባሰብ አሻራቸውን አሳርፈዋል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ድሉ በአንድ ወገን ብቻ የተገኘ ሳይሆን የቀደመው ትውልድ ከሁሉም አቅጣጫ ተንቀሳቅሶ ዋጋ የከፈለበት ነው ብለዋል፡፡
ከጾታ አኳያም ከወንዶች እኩል ጦር ሜዳ ተገኝተው በጎራዴ የመዋጋታቸውን ያክል ምግብ በማብሰልና ለደከመው ሞራል በመስጠት የተሳተፉት ሴቶች ቁጥር በቀላሉ የማይገመት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህ በከፍተኛ ገድል የተገኘው የአድዋ ድል ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ጎልታ እንድትታይ አስተዋጽኦ አድርጓል ብሏል፡፡
አፍሪካውያን ከጦርነቱ በፊት በምዕራባዊያን ዘንድ እንደሰው የማይቆጠሩበት ጊዜ እንደነበር የጠቀሰው ገጣሚና ጸሃፊ-ተውኔት አያልነህ ከድሉ በኋላ ግን ይህ አይነት አስተሳሰብ እንዲሰበር ሆኗል ነው ያለው፡፡
የአድዋ ድል በአፍሪካውያን ዘንድ ብሔራዊ ስሜት እንዲፈጠር በማድረግ ፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ እንዲጀመርና እንዲመሰረት የማይናቅ ሚና መወጣቱም ተመልክቷል፡፡