ቀጥታ፡

የአዘርባጃን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማሩ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 22/2015 የአዘርባጃን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ።

አቶ ደመቀ መኮንን ነገ በሚጀመረው የገለልተኛ አገራት ንቅናቄ ወይም (Non-Aligned Movement) ስብስባ ለመሳተፍ ትናንት አዘርባጃን መግባታቸው ይታወቃል።

ከአዘርባጃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄይሁን ባይራሞቭ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።


ኢትዮጵያ በመከላከያ፣ደህንነት፣ በቴክኖሎጂ አማካኝነት በሚደረግ የአቅም ግንባታ እና ‘ፐብሊክ ሴክተር’ መስኮች ከአዘርባጃን ጋር በትብብር መስራት እንደምትፈልግ አቶ ደመቀ ገልጸዋል።


የአዘርባጀን ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።


የአዘርባጃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄይሁን ባይራሞቭ የሰሜን ኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት የታየውን ኃላፊነት የተሞላውን የአመራር ሰጪነት አድንቀዋል።


የኢትዮጵያ ተማሪዎች በአዘርባጃን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲማሩ የምትሰጠውን እድል አጠናክራ እንደምትቀጥል መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።


የገለልተኛ አገራት ንቅናቄ (Non-Aligned Movement) እ.አ.አ 1961 የተቋቋመ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው።


ድርጅቱ በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት ፍላጎቶች እና ሕልሞች እንዲሳኩ መስራት ዋንኛ አላማው ነው።


ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ100 በላይ አገራት የንቅናቄው አባል አገራት ናቸው።


አዘርባጃን የወቅቱ የንቅናቄው ሊቀ መንበር ናት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም