ከአድዋ ጀግኖች በአንድነት ለነጻነት መቆምን በመውረስ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በጋራ መስራት አለብን - ዶክተር አብርሃም በላይ - ኢዜአ አማርኛ
ከአድዋ ጀግኖች በአንድነት ለነጻነት መቆምን በመውረስ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በጋራ መስራት አለብን - ዶክተር አብርሃም በላይ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 22/2015 ከአድዋ ጀግኖች በአንድነት ለነጻነት መቆምን በመውረስ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በጋራ መስራት አለብን ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ገለጹ።
የመከላከያ ሚኒስቴር 127ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን ምክንያት በማድረግ ያዘጋጀው አገር አቀፍ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ፤ አድዋ የኢትዮጵያዊያንን ተክለ-ስብዕና እና የአሸናፊነት ስነ-ልቦና ለዓለም የገለጠ ድል መሆኑን ገልጸዋል።
ድሉ የወቅቱ ኃያላን አገራት በአፍሪካ ላይ የነበራቸውን የተዛባ እሳቤ የቀየረ የመጀመሪያው ታሪካዊ ክስተት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም አፍሪካዊያንና የጥቁር ህዝቦች የፀረ ጭቆና ንቅናቄን እንዲያቀጣጥሉ እርሾ መሆኑንም ገልጸዋል።
በመሆኑም የአድዋ ድልን በአግባቡ ከመዘከር ባሻገር ለሀገር ግንባታ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን የጋራ ድል መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የአሁኑ ትውልድ ከአድዋ ድል ጀግኖች በመማር የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በጋራ መቆም እንዳለበት መክረዋል፡፡
ትውልዱ የአድዋ ድልን እና ጀግኖችን በመዘከር የራሱን አድዋ በየዘርፉ መድገም ይኖርበታል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በአድዋ ድል ያስከበረችውን ማንነትና ሉዓላዊነት አጠናክራ እንድትቀጥል የምግብ ዋስትናንና ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በውይይቱ ጥናታዊ ፅሑፍ ያቀረቡት የታሪክ ተመራማሪው ዶክተር አየለ በከሪ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሺህ ዘመናት የነበረው አብሮነትና በሀገር ጉዳይ በአንድ የመሰለፍ ባህል በአድዋ ድል በደም አሻራ መታተሙን ገልጸዋል።
ከጦርነቱ በፊትና በጦርነቱ ወቅት ኢትዮጵያውያንን ለመከፋፈል የተደረገው ጥረት ለሀገራቸው ግንባራቸውን በሰጡ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን መክሸፉንም ጠቅሰዋል።
100 ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን ከአራቱም ማዕዘን በጋራ በመዝመት የካቲት 23 ቀን 1888 ባስመዘገቡት ድል ቀና ብለን እንድንሄድ አድርገውናል ነው ያሉት።
በመሆኑም የዚህ ዘመን ትውልድ የአድዋ ጀግኖች በክብር ያስረከቡትን ሀገር ወደ ተሻለ ከፍታ በማሸጋገር በኩል ትልቅ የቤት ስራ እንዳለበት በማንሳት።
የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፤ "ዓድዋ የነፃነታችን መሠረት የጥቁር ሕዝብ ኩራት" በሚል ባቀረቡት ፅሑፍ፥ ዓድዋ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ከዚያም የዓለም ጭቁኖች ድል በመሆኑ አድማስ የለሽና ወደር የለሽ ነው ብለዋል።
በአድዋ የተገኘው ድል የዓለምን አተያይ የቀየረ ስለመሆኑ የተናገሩት ተመራማሪው፤ የድሉ ምስጢር "የኢትዮጵያዊያን አንድነትና ትስስር ነው" ይላሉ።
በዚህም በመላው ዓለም የፀረ ጭቆና ትግልን እንዲሁም በአፍሪካ የፀረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄን በማቀጣጠል ረገድ አርዓያ ተደርጎ መወሰዱን ነው የጠቀሱት።
ይህንን ድል አፍሪካዊ ድል ሆኖ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ሊዘከር እንደሚገባም አንስተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የአድዋን ጦርነት፣ የተመራበት ወታደራዊ ስልትና ማህበራዊ መስተጋብር በዘመናዊ የጦር ግንባታ ውስጥ በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ድሉ የአንድነት፣ የፅናትና የጀግንነት ምልክት በመሆኑ በዚህ ዘመንም አንድነታችንን በማጠናከር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የአድዋ ጀግኖች ቅራኔዎች ሳይገድባቸው ካሳዩት መግባባት ትምህርት በመውሰድ ጠንካራ ሀገር በጋራ መገንባት እንደሚገባ ተናግረዋል።