በካማሺ ዞን በመንገድ መዘጋት ምክንያት ለተፈናቃዮች ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ አልተቻለም - ኢዜአ አማርኛ
በካማሺ ዞን በመንገድ መዘጋት ምክንያት ለተፈናቃዮች ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ አልተቻለም
አሶሳ መስከረም 26/2011 በቤኒሻንጉል ጉመዝ ክልል ካማሽ ዞን ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከአካባቢያቸው ለተፈናቀሉ ሰዎች በመንገድ መዘጋት ምክንያት ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ አለመቻሉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ፡፡ ህብረተሰቡ ላይ ጥቃት ለመፈጸም በክልሉ ውስጥ በድብቅ ወታደራዊ ስልጠና ሲያካሂዱ የነበሩ አካላት እንዳሉ ፖሊስ የደረሰበት መሆኑንም ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰይፈዲን ሃሩን ዛሬ እንደገለጹት በክልሉ መስከረም 16 ቀን 2011 ዓ.ም በዞኑ አመራሮች ላይ በታጠቁ ኃይሎች የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ በተከሰተ ግጭት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው ተፈናቅለዋል። የተፈናቀዮች ቁጥር በየጊዜው ቢጨምረም በአካባቢው የሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ፖሊስ አባላት ህበረተሰቡን የማረጋጋት ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወደ ካማሺ ዞን የሚያስገቡት መንገዶችን ጨምሮ ከአሶሳ ወደ አዲስ አበባና ቶንጎ ከተሞች የሚደረገው ጉዞ መስተጓጎሉን የገለጹት ኮሚሽነሩ በመንገድ መዘጋት ምክንያት በካማሺ ዞን ሦስት ወረዳዎች ተጠልለው ለሚገኙ ተፈናቃዮቹ የምግብ፣ የመጠለያና ሌሎች የሠብዓዊ አገልግሎቶች ድጋፍ ለማድረግ አለመቻሉን ተናግረዋል ኮሚሽነር ሰይፈዲን እንደሚሉት ችግሩን ያስከተለው የታጠቀ ኃይል ከጸጥታ ኃይሎች አቅም በላይ በመሆኑ ሳይሆን ሠላማዊ ዜጋ በመምሰል ህብረተሰቡ ውስጥ በመሸሸጉ ነው፡፡ ከሰብዓዊ ድጋፍ በተጨማሪ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ለማድረስ አልተቻለም ያሉት ኮሚሽነሩ፣ በዞኑ ሠላማዊ በሆኑ ሌሎች አካባቢዎችም ለቤት ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ ሸቀጦች በመንገድ መዘጋት ምክንያት እየገቡ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ “ በግጭቱ የተጎዱት የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ነዋሪዎች ናቸው ” ያሉት ኮሚሽነር ሰይፈዲን በአሁኑ ወቅት ሁለቱም ህዝቦች አንዳቸው ለሌላቸው ከለላ በመስጠት ከጥቃት እየተከላከሉ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በሌላ በኩል ህብረተቡ ላይ ጥፋት ለማድረስ በክልሉ በድብቅ ጫካ ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና ሲያካሂዱ የነበሩ ግለሰቦች እንዳሉ ፖሊስ እንደደረሰብት ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡ ጉዳዩ በምርመራ ላይ በመሆኑ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ገልጸዋል፡፡ “ በአሶሳ ነዋሪዎች ዘንድ የሚታየው የደህንነት ሥጋት ሀገራዊ ለውጡን በማይፈልጉ አካላትና ግጭቶችን መሠረት አድርገው ዘረፋ በሚያካዱ ግለሠቦች የተፈጠረ ነው ” ሲሉም አስታውቀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ህዝቡን የማረጋጋት ሥራ እየተሰራ በመሆኑ ነዋሪዎች ከሥጋት ወጥቶ ለአካባቢው ሠላም ከጸጥታ አካላት ጋር ተባብሮ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡