ነፃ የትምህርት ዕድሉ ኢትዮጵያን በተሻለ መልኩ ለማገልገል ዕድል የሚሰጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ነፃ የትምህርት ዕድሉ ኢትዮጵያን በተሻለ መልኩ ለማገልገል ዕድል የሚሰጥ ነው

የካቲት 22/20215 /ኢዜአ/ የውጭ ትምህርት ዕድሉ ያልጠበቁት ከመሆኑም በላይ አገራቸውን ለማገልገል እድል እንደሚሰጣቸው የዘንድሮውን የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ከፍተኛ ነጥብ በስመዝገብ እውቅና የተሰጣቸው ተማሪዎች ገለጹ።
ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ተፈትነው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ትላንት ማምሻውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚሁ ጊዜ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ 273 ተማሪዎች በተባበሩት አረብ ኤምሬት ሙሉ የትምህርት ዕድል ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል።
እውቅና ከተሰጣቸው ተማሪዎች መካከል ከአሰላ ኤዲ ኤም ትምህርት ቤት 650 በማስመዝገብ ከሴቶች አንደኛ ውጤት ያገኘችው ናሆሚን ደንበል አንዷ ናት።
ውጤቱን ለማግኘት ብዙ ሰርቻለሁ የምትለው ተማሪ ናሆሚን “ከበፊትም ማንበብ እወዳለሁ ለ12ኛ ክፍል ፈተና በተሻለ መልኩ ዝግጅት በማድረጌም ለውጤት በቅቻለሁ ነው” ያለችው።
ለተገኘው ውጤት በአገር አቀፍ ደረጃ እውቅና ማግኘቴ የፈጠረብኝ ስሜት በቃላት የሚገለጽ አይደለም፤ በተለይ የውጭ የትምህርት ዕድል መመቻቸቱ ደግሞ ያልጠበቅነው ነው ስትልም ነው የተናገረችው።
ኤሮ ስፔስ ኢንጂነር የመሆን ሕልም እንዳላት ገልጻ፤ ሕልሟን ለማሳካት የትምህርት ዕድሉ መልካም አጋጣሚ እንደሚሆንም ጠቁማለች።
ተማሪ ናሆሚን ወደ ፊት በምትሰማራው መስክ ለኢትዮጵያ የተሻለ ነገር የማበርከት ሃሳብ መሰነቋንም ነው የተናገረችው።

የተማሪ ናሆሚን ወላጅ አባት አቶ ደንበል ገመዳ እንዳሉት፤ ልጃቸው ካገኘችው ውጤት ባሻገር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እጅ ሽልማት መቀበሏ ደስታቸውን እጥፍ ድርብ እንዳደረገው ገልጸዋል።
ከደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት 666 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ተማሪ ሚኪያስ አዳነ ከሁሉም የላቀ ውጤት በማምጣት ተሸላሚ ሆኗል።

በትምህርት ቤቱ ውድድር ያለ በመሆኑ ሁሌም ዝግጁ ነኝ ጠንክሬ በመማሬ ለውጤት በቅቻለሁ ያለ ሲሆን እውቅናው የድካማችን ፍሬ በመሆኑ ተደስቻለሁ ብሏል።
ከእውቅናው ጎን ለጎንም የውጭ የትምህርት ዕድል መመቻቸቱ ሌሎች ተማሪዎችን የሚያበረታታ ተግባር መሆኑንም አንስቷል።
የተማሪ ሚኪያስ አዳነ ወላጅ እናት ወይዘሮ ሙሉወርቅ ደርሶ፤ ተማሪ ሚኪያስ ለውጤት ያበቃው በራሱ ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ የወላጅና መምህራን እንክብካቤ በመኖሩ ነው ብለዋል።

ወላጆች ተማሪዎች ከመስመር እንዳይወጡ ክትትል ማድረግ እንዳለባቸውም መክረዋል።
እውቅና የተሰጣቸው ሌሎች ተማሪዎችም በሰጡት አስተያየት እውቅናው የበለጠ ጠንክረን እንድንማር ያነሳሳ ነው ብለዋል።
በውጭ በሚኖረን የትምህርት ቆይታ ተፈላጊውን ዕውቀት ጎብኝተን አገርና ሕዝብ የሚያኮራ ስራ ለማከናወን ዝግጁ ነን ሲሉም ነው የተናገሩት።

ሌላው አስተያየት ሰጪ ተማሪ ቅዱስ እዮብ ከአዲስ አበባ ስኩል ኦፍ አይጎዳ በተፈጥሮ ሳይንስ ከፍተኛ ውጤት በማጣት ለእውቅና በቅቷል።
ቀጣይ 12ኛ ክፍል የሚፈተኑ ተማሪዎች ውጤታማ ለመሆን ጥረት ማድረግ አለባቸው ትምህርት ላይ ትኩረት እንዳያደርጉ ከሚያዘናጉ ጉዳዮች ራሳቸው ማቀብ እንደሚኖርባቸውም አስገንዝቧል።
የተሰጠን እውቅና በቀጣይ የትምህርት ዘመናችን የበለጠ መናሳሳት ፈጥሮብናል ያለው ደግሞ ከኦሮሚያ ልማት ማህበር ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የመጣው ተማሪ አበራ ነው።