የአድዋ ድል የዓለምን የጥቁር ህዝቦች ታሪክ የቀየረ አስደማሚ ሁነት ነው--የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል የዓለምን የጥቁር ህዝቦች ታሪክ የቀየረ አስደማሚ ሁነት ነው--የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 22/2015 የአድዋ ድል የዓለምን የጥቁር ህዝቦች ታሪክ የቀየረ አስደማሚ ሁነት ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
አፈ-ጉባኤው 127ኛውን የዓድዋ ድል በዓል አስመልክቶ ለመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባስተላለፉት መልዕክት የዓድዋ ድል ብዝኀ ማንነቶች ለአንድ ዓላማ ተሰልፈው የማይሰበር የሚመስለውን የአውሮፓን የቅኝ ግዛት ቀንበር እንዳይፈራርስ ሆኖ ለዘመናት የተገነባውን የሮማንን ኢምፓየር በሚያስደንቅ ጀብዱ የአንኮታኮቱበት አስደናቂ የታሪክ ክስተት እንደሆነ ገልጸዋል።
የያኔው ትውልድ አንጸባራቂውን ድል የተቀናጁት በዘመናዊ የጦር መሣሪያ ታግዘውና በወታደራዊ ሳይንስ ተክነው ሳይሆን ይልቁንም አንድነታቸው ጉልበት፣ የሀገር ፍቅር ስሜታቸው ስንቅ፣ የአያት ቅድመ አያቶቻቸው የጀግንነት ታሪክ ወኔና ጥበብ ሆኗቸው ነው ብለዋል።
በዚህ የጦር ግንባር ውሎ አንድነት ከዘመናዊ የጦር መሣሪያ በልጦ ታይቷል፤ የሀገር ፍቅር ስሜት ከወታደራዊ ሳይንስ ልቆ ተገኝቷል ብለዋል።
ጥቁርነት ጽናት፣ ኢትዮጵያነት ደግሞ ኩራት መሆኑን ዓለም ምስክርነቱን እንዲሰጥ ሆኗል ያሉት አቶ አገኘሁ የእንግሊዝ ጋዜጦች እንኳን በፊት ገጻቸው የዓለም ታሪክ ተገለበጠ፤ ታላቅ የትውልድ ኃይል በአፍሪቃ ተቀሰቀሰ ብለው እንዲጽፉም ተገደዋል፡ ሲሉም ገልጸዋል።
የአድዋን ድል ስናከብርም ሆነ ስናስታውስ ንጉሥ ምኒልክንና እቴጌ ጣይቱን እንዲሁም ጀግኖች የጦር አበጋዞቻቸውን መዘከር እንደሚገባም አስረድተዋል።
የአሁኑ ትውልድ የነበሩትንና ያሉትን መልካም ተሞክሮዎች በማበራከት፣ ጠንካራ አገራዊ አንድነትን በማጽናት የግዛት አንድነቷ የተከበረ፣ ልማቷ የተፋጠነ፣ ሰላሟ የተጠበቀና ለሁሉም ዜጎች የምትመች ሕብረብሔራዊት ኢትዮጵያን በመገንባት የራሱን አኩሪ ታሪክ ሠርቶ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅበታል ብለዋል።
በመልዕክታቸው የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ድምር ውጤት ነው ያሉት አፈ-ጉባኤው ዓድዋ ላይ ኢትዮጵያውያን የቋንቋ፣ የሃይማኖትና የባህል ብዝኀነት ሳይለያያቸው፣ ውስጣዊ ችግሮቻቸው የጥል ግድግዳ ፈጥረው ሳያስቸግሯቸው አንዳቸው ለሌላቸው ቆስለዋል ክቡር ሕይወታቸውንም ሰውተዋል፤ በደማቸው የአብሮነትን ቃል ኪዳናቸውን እንዳጸኑ ገልጸዋል፡፡
በአጥንታቸው ክስካሽ ኢትዮጵያዊነትን በጽኑ መሠረት ላይ ማቆማቸውን ገልጸው የግንኙነታቸው ውል በአላፊ ነፋስ እንዳይገፋ፣ በአሉባልታ ወሬ እንዳይፈታ አድርገው አስረውታል፡፡ የጋራ ታሪካቸውንም በዘመን እንዳይገታ አድርገውታል ብለዋል።
የዓድዋ ድል ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን የፅናት አብነት፣ የኩራት ምንጭና የ“የይቻላል” ወኔን የሰነቅንበትና በዓለም አደባባይ ቀና ብለን እንድንታይ ያስቻለን መሆኑንም ገልጸዋል።
ድሉ በጨለማው የጥቁሮች ሰማይ ስር የነጻነትን ብርሐን የከሰተ አብሪ ኮከብ እንደሆነ ገልጸው የዓለምን ታሪክ የቀየረ አስደማሚ ሁነትም ነው፤ ኢትዮጵያ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ያበረከተችው ስጦታና ለነጻነት ትግሉ ፋናወጊ ሆኖ የመራ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ስንቆም ከራሳችን አልፈን ለሌሎች ወንድሞቻችን ፋናወጊ እንሆናለን፤ ለዓለምም የምናበረክተው መልካም ስጦታም ይኖረናል ሲሉ በመልዕክታቸው ገልጸዋል።
በመሆኑም የዓድዋን የድል በአል ስናከብር በእኩልነት፣ በአብሮነት፣ በፍቅርና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባል በማለት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።