አድዋ የፓን አፍሪካዊነት እርሾ..

 (አየለ ያረጋል) 

መንደርደሪያ  

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የዛሬው አፍሪካ ሕብረት) ከተመሰረተ ዘንድሮ 60 ዓመታት ደፈነ።

አፍሪካ ሕብረት በ2063 ለማሳካት ያቀዳቸው አህጉር አቀፍ ግቦች ትግበራ 10ኛ ዓመታት ሞልቶታል።

36ኛው የአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ጉባዔ 'የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ትግበራን ማፋጠን' በሚል መሪ ሃሳብ መካሄዱ በርካታ ፓን አፍሪካዊያን ዘንድ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል።

ይሄውም የቀደምት አፍሪካዊያን ፖለቲካዊ ግቦች ወደ አፍሪካ አቀፍ ምጣኔ ሀብታዊ ሕልሞች ስኬት መንገድ ይመራል የሚል ብሩህ ተስፋ በማሳየቱ ነው። ቀደምት ፓን አፍሪካዊያን መሪዎች ሲሰባሰቡ አፍሪካን ከቅኝ ገዝዎች መንጋጋ ፈልቅቀው ነጻነቷ የተረጋገጠ፣ የዳበረችና ሕብረቷ የተጠበቀ አፍሪካን ዕውን ለማድረግ በመሻት ነበር።

በዚህም ከአውሮፓዊያን ቅኝ ግዛት ቀድመው ነጻነታቸውን ያወጁ ሀገራት፤ ይህን ሕልማቸውን ዕውን ለማድረግ ድርጅት ሲጠነስሱ የሀሳብ ሜዳና መዳረሻቸው ኢትዮጵያ ነበረች። ለምን ቢሉ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻነት ዘፍጥረት ነጸብራቅ ናትና።

ይሄ የሆነው ታዲያ በአድዋ እርሾ ላይ ተመስርቶ ነው። "አድዋ ድል የአፍሪካ ድል ነው። የኢትዮጵያ ትንሳኤ የአፍሪካ ትንሳኤ ነው" እንዲሉ የፓን አፍሪካዊነት አቀንቃኙ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት።  

አፍሪካ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መልከ ብዙ ፈተናዎች እየተናጠች ቀጥላለች። በየጊዜው ወደ አስከፊ ድህነትና ውስጣዊ መከፋፈል ቀውስ እያመራች ባለበት አሁናዊ መልኳ የአፍሪካ ሕብረት ህልሞች ይሳካሉ ወይ የሚለው የብዙሃኑ ስጋት ነው።

እናም የፓን አፍሪካዊነት (Pan Africanism) እርሾ የሆነውን አድዋ ድልን ተጠቅሞ መነጋገር፤ የአፍሪካ እንጀራዋን መጋገርና ዕቅዷን መተግበር ሳያሻት አይቀርም። 

 የአድዋ ድል የፓን አፍሪካዊነት እርሾነት 

(…) “አድዋ የደም ግብር ነው፤ አበው የለኮሱት ቀንዲልአድዋ የአፍሪካ ዱካ ነው፤ አበሽ የከተበው ፊደልላጥፋህ ቢሉት መች ይጠፋል፤ ጠላት በልቶ ያፈራ ተክልለዛሬም ታሪክ ነው፣ ‘ነገም ሌላ ቀን ነው’ ለሚል…”(ከደራሲና ጋዜጠኛ ነብይ መኮነን ‘ስውር ስፌት’ ከተሰኘው የግጥም መድብል የተቀነጨበ)

የአድዋ ጦርነት ሰበብ የውጫሌ ውል ነው የሚለው ታሪካዊ ዕይታ ሰፊ ቦታ ይዟል።

ዳሩ አሳማኙ የጦርነቱ መንስኤ ከውጫሌ ውል ይልቅ አፍሪካን በይፋ የመቀራመት ውሳኔ የተደረገበት በርሊን ጉባዔ ነው የሚል ምሁራዊ አተያይ አለ። ጉባዔው አፍሪካዊያንን ለዘመናት በባርነት ሲያግዙ የኖሩ አውሮፓዊያን አፍሪካዊያንን እንደ ሸቀጥ ከመጠቀም ባሻገር ሁለመና አንጡራ ሀብት ለመበዝበዝ የሜድትራኒያንን ባህር ተሻግረው አፍሪካን ለመቀራመት በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ያደረጉት ስምምነት ነበር።

የኢትዮጵያ ዕጣም ለኢጣሊያ መንግስት ወጥቷል። 

አንዳንድ የታሪክ አተያዮች አጼ ዮሐንስ መተማ ላይ በተሰው በጥቂት ቀናት ልዩነት የተፈረመው የውጫሌ ውል ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ዙፋን ከተረከቡ በኋላ ራሳቸውን እስኪያደራጁ ለጊዜ መግዣ ያደረጉት ውል እንጂ ጦርነቱ አይቀሬነት ንጉሱ መጠርጠራቸው አልቀረም ይላሉ።

ለዚህ ደግሞ የአድዋ ጦርነት የተደረገው የውጫሌ ውል ከተፈረመ ከአምስት ዓመታት በኋላ መሆኑ፤ በርግጥም አድዋ ጦርነት የበርሊን ጉባዔ ውሳኔ ጦስ እንጂ የውጫሌ ብቻ አይደለም የሚለው ሃሳብ ገዥነት ይኖረዋል።

የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪ የአፍሪካ ቀን በተከበረበት በአንድ ወቅት "ከአድዋ ድል 11 ዓመታት ቀደም ብሎ በርሊን ላይ በተደረገው አፍሪካን የመቀራመት ጉባዔ፤ ከአድዋ ድል ማግስት ፉርሽ ሆነ።

የበርሊን ጉባዔ ውሳኔ ወደ ግጭት እንዲያመሩ አደረጋቸው።

አፍሪካ ቅኝ መገዛት አለባት የሚለውን እሳቤ ኢትዮጵያ በእምቢተኝነት ተቃወመች፤ በገቢርም አሳካቸው።

ከተባበሩ ማንንም ሃይል ማሸነፍ እንደሚቻል ለአፍሪካዊያን ግልጽ መልዕክት አስተጋባች" በማለት አብራርተው ነበር።  

ቅድመ አድዋ የኢጣሊያን ጦር አዝማች ጄነራል ባራቴሪ ምኒልክን ጉሮሮውን አንቆ ወደ ኢጣሊያ ሀገር እንስሳት ማቆያ እንደሚያመጣው ለሀገሪቷ ምክር ቤትና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ክሪስፒ ፊት ቃል ገብቶ ነበር። ከወራት በኋላ በተደረገው የአድዋ ጦርነት ግን ነገሩ የተገላቢጦሽ ነበር።

የኢጣሊያ ወራሪ ጦር አድዋ ላይ የሽንፈት ካባ ተከናንቦ ተመለሰ።

ጀኔራል ባራቴሪም ‘ጽድቁ ቀርቶ በቅጥ በኮነነኝ’ እንዲሉ በጦርነቱ ተዋርዶ የጀኔራል መኮነንነት ማዕረጉ ተገፎ የተጠያቂነት ፍርድ ተፈረደበት።

 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ኤምሬትስ ፕሮፌሰሩ ባህሩ ዘውዴ በአንድ ወቅት የአድዋ ክብረ በዓል ላይ ባቀረቡት ጽሁፍ “ጥቁር ሕዝቦች ከነጮች ጋር ያደረጓቸው ጦርነቶች ብዛት የትየሌለ ነው። አንድም ጦርነት ግን በነጮች ላይ ድል አልተጎናጸፈም፤ ከወርቃማው የአድዋ ድል በስተቀር” ማለታቸውን አስታውሳለሁ።

በፕሮፌሰሩ አተያይ አድዋ አዲስ የታሪክ ምዕራፉ ሲከፍት በአንጻሩ ነባር አስተሳስብ ሰብሯል፤ የጥቁሮች የበታችነት ስሜትና የነጮች የበላይነት አስተሳስብ ለመጀመሪያ ጊዜ በአድዋ ተራሮች ግርጌ ተሽሯል።

ፕሮፌሰሩ ‘ኢትዮጵያዊያን ለምን አሸነፉ’ የሚለው አመክንዮ ሲፈትቱም ቅድመ አድዋ ጦርነቶች ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለልዩነት ህብረት መቆሙ፤ የአጼ ምኒልክ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንዲሁም በጦርነቱ ወቅት የነበረው የኢትዮጵያዊያን ታክቲካዊ የበላይነት እንደሆነ ይገልጻሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በአንድ ወቅት “ታሪክን ለሚመረምር ትውልድ ዓድዋ ውስጥ ሕልውናን አፅንቶ የመኖር፣ ዓድዋ ውስጥ ዲፕሎማሲ፣ ዓድዋ ውስጥ ወታደራዊ ስትራቴጂ፣ ታላቅ ውስጣዊ የሕዝቦች ኅብረትና አንድነት፣ ጥበብና ተግባቦት፣ ፍቅርና መስጠት፣ ክብርና ጀግንነት ሞልቶና ሰፍቶ የነበረ መሆኑን እናያለን” ብለው ነበር።የአድዋ ድል ቱርፋቶች መልከ ብዙ፣ ቀለመ ደማቅ፣ አድማስ ዘለል ናቸው።

አድዋ አገራዊ፣ አህጉራዊና ሉላዊ እሳቤን ለውጧል። በዚህ ጽሁፍ ግን የአድዋ ድል ቱርፋትን ከፓን አፍሪካዊነት አተያይ እንቃኛለን። አድዋ ድል ከኢትዮጵያዊያን ባለፈ ለለቀረው አፍሪካ፣ ሰፋ ሲልም ለመላው ጥቁር ሰብዓ ዘር ምን ፈየደ፤ ምንስ አተረፈ፣ ለኋላው ፓን አፍሪካዊነት ምን አበርክቶ ነበረው የሚሉ ተጠየቆች ሲፈተኙ ለዛሬዋና ለነገዋ አፍሪካ የሚበጁ ቁም ነገሮችን ነቅሶ ማውጣት ይቻላል። 

የአሜሪካው ሞርጋን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪው ዶክተር ጌታቸው መታፈሪያ የአድዋ ድል “አንድም ቅኝ ገዥዎች ኃያልነታቸው በአፍሪካዊያን እንደሚፈተን የተገነዘቡበት፤ ሁለትም የአፍሪካ ዳያስፖራዎች የተስፋ ስንቅ የታጠቁበት ነው። ባርነት፣ ጭቆና፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ብዝበዛዎች እልባት እንዲያገኙ ደወል አቃጭሏል። ልክ ዳግማዊ ምኒልክ ኢትዮጵያዊያንን ካለአንዳች ልዩነት አሰባስበው ጠላትን ድል እንደነሱት ሁሉ አርቆ አሳቢ አመራር ካለ አፍሪካዊያን እኩልነት፣ ፍትሕና የህልም እንጀራ የሆነባቸውን ሁለንተናዊ አህጉራዊ ሠላም ማግኘት እንደሚችል ወኔ ቆሰቆሰባቸው” ብለዋል።

ዕውቁ የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት “የአድዋ ድል ዜና በአውሮጳ ኃያላን ዘንድ የጦር አደጋ ጋረጠ፤ ሮምን በመሰሉ የአውሮጳ ከተሞች የፖለቲካዊ ቀውስ ምጽዓት ቀረበ፤ የእንግሊዛዊያንን ሸውራራ እሳቤም በአንድ ሌሊት ቀየረ” ይላሉ።

እንደ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ጥናት አድዋ ከትግል ባሻገር በደቡብ አፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካ ‘ኢትዮጵያዊነት’ የሚል ሃይማኖት አስተምሮ እንቅስቃሴ ያስጀመረ ታሪካዊ ከስተትም ነው።

በአድዋ ድል ማግስት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በኢትዮጵያ ስም አያሌ አብያተ- ክርስቲያናት መታነጻቸውን ይዘረዝራሉ። ለአብነትም የተባበሩት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ተልዕኮ በደቡብ አፍሪካ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ አፍሪካ፣ የቅዱስ ፍሊፕ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ አፍሪካ፣ የኢትዮጵያ የምህላ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ አፍሪካ እና የኢትዮጵያ ሰብዓ-ገነት የእግዚአብሄር መመስገኛ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚሉት ይገኙበታል።

በተመሳሳይ የሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር ሃሮልድ ማርክስ “ለጥቁር ዳያስፖራዎች የኢትዮጵያ ድል ጮራ የወቅቱ ክብርና ለነጋቸው የይቻላል መንፈስ ያስታጠቃቸው ልዩ ክስተት ሆነም” ይላሉ።

ምዕራባዊያኑ በጥቁሮች ላይ ለዘመናት ያሳደሩትን ጥላቻ፣ ዘረኝነት፣ ንቀት እንዲያጤኑ፤ ማድረጉን ይጠቅሳሉ። በኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪው ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በበኩላቸው አድዋን ልዕለ አውራጃዊ ምልከታ፣ ልዕለ ዘውግ አስተሳስብ የታየበት የጋራ ነጻነት ዓርማ ሲያደርጉት፤ ዕውቁ የታሪክ ሰው ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌታሁን ድሌቦም አድዋን 'ኢምፔሪያሊዝምን ያሸነፈ ድል' በማለት ገልጸውታል።

‘የአድዋ ጦርነት’ በተሰኘው መፅሀፋቸው የሚታወቁት ፕሮፌሰሩ ሬሞንድ ጆናስ አንዳንድ የምዕራባዊያን አገራት የአድዋን ድል ለማንኳሰስ ቢሞክሩም ሙከራው ወንዝ እንዳላሻገራቸው ይጠቅሳሉ።

‘ታሪክ የተለየ ክስተትን ይወዳል’ የሚሉት ፕሮፌሰሩ አድዋ ተለምዷዊ ጉዞ የቀየሰ፣ ነባር ንግርን የለወጠ፣ ለአፍሪካዊያን ቅኝ ተገዥዎች የራስ መተማመን ጉልበት ያጎናጸፈ፣ በአጠቃላይ አድዋን የታሪክ ዑደትን የጨዋታ ሕግ የቀየረ ዕውነታ አድርገውታል።

ፕሮፌሰሩ አክለውም ከአድዋ ድል ቱርፋት ሀተታቸው አድዋ አፍሪካን በዝባዥ ወራሪ ሃይልን ያስተማረ፣ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች በመላው ዓለም በበረቱበት በዛ ወቅት አጼ ምኒልክ ለምርኮኞቻቸው ያሳዩትን ርህራሄና ህዝቡን አስተባብሮ የመምራት ብልሀተቻው የታየበት ከዚህም ባሻገር ግን ለአፍሪካውያን ብሎም ለአፍሪካ አሜሪካውያን የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ምልክት እና ለፓን አፍሪካን ራዕይ አቀንቃኞች ተምሳሌት ድል መሆኑን ጠቅሰዋል።

የካናዳው ማክጊል ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ምሁር ዶክተር ሜማይሬ ሜናሴማይ፤ አድዋ የማይቻል መሰል እውነት በገሃድ የታየበት ሁነት ነው፤ አዲስ ፖለቲካዊ ተጠየቅ የፈለቀበት፤ ታሪካዊ አድማስ የተከፈተበትም ዕለት እንደሆነ የሌሎች ምሁራንን ሃሳብ ይጋራሉ።

በኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ፣ ባሕልና አወቃቀር ጥናታቸው በስፋት የሚታወቁት ፕሮፌሰር ዶናልድ ሊቨን የአድዋ ዘመቻ ድል ፍሬ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን የሚሊዮን ጥቁሮች የኩራትና ወኔ ፏፏቴ ቅርስ እንደሆነ ይገልጻሉ። አድዋ ከአፍሪካዊያን ንቅናቄ መነሻነቱ ባሻገርም ለጥቁሮች መብት ታጋዩ ማርክስ ጋርቬይ “ኢትዮጵያ እውነተኛዋ የአባቶቻችን ምድር” በማለት ለ‘የምልሰተ አፍሪካ ንቅናቄ’ ቅስቀሳው ተጠቅሞበታል።

እውቅ የጥቁር መብት ተሟጋቾች የሃይቲው ቤንቶ ሲልቫን፣ የምዕራብ ኢንዲያኖች ጆሴፍ ቪታሌን፣ እንዲሁም ቡከር ዋሽንግተን፣ ኢዳ ዌልስ፣ ዲ ቦይስ ‘የጺዮን ንጉስ’ ምልክት በማድረግ ለፀረ ቅኝ ግዛትና ዘረኝነት ትግል ቀስቅሰውበታል።

በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ከነበሩ የአፍሪካና የላቲን አሜሪካ አገራት የነጻነት ታጋዮች መካከልም የናይጄሪያው ናምዲ አዝኪዌ፣ የጋናው ክዋሜ ንኩርማን፣ የኬንያው ጆሞ ኬንያታ፣ የጀማይካው ጆርጅ ፓድሞሬ በአድዋ ድል ዜጎቻቸውን በመቀስቀስና ከጎናቸው በማሳለፍ፣ ተከታዮችን አፍርተዋል።

በአጠቃላይ ድሕረ አድዋ ድል ኢትዪጵያ ውስጥ ዘመናዊነት እንዲስፋፋ፣ የባቡር፣ ስልክ፣ ትምህርት፣ ፖስታ፣ ቴሌ፣ መንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲዘረጉ፤ ኢትዮጵያ የትኛውም አፍሪካዊ አገር ያላገኘውን የራሷን የፖለቲካ ኢኮኖሚ እንድትመራ አስችሏታል።

ታላቁ የአድዋ ድል ዘመናዊት ኢትዮጵያን ከጥንታዊ ታሪኳ ጋር ያዋደደ፤ የጥንቶቹን አባቶቻችን ጀግንነትና ለአገር ያላቸውን ፍቅር ያስመሰከረ፣ የነጻነት አይበገሬነት ወኔን ያሳዬ፣ የህዝቦች አንድነት ህያው ማሳያ ታሪካዊ ሁነት ነው።  እናም አድዋ ለ’ፓን አፍሪካዊነት’ ጉዞ መሰረት ሆኗል፤ ቅኝ ግዛት እጣፈንታ አለመሆኑን አብስሯል። በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ቀንበር ሲላቀቁ ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለማትን ተሻምተዋል።

አድዋ በሌሎች አገሮች ሕዝቦች የነጻነት ትግል ተምሳሌት ሆኖ በተለይም የጥቁር ዓለም ህዝቦችን ያነሳሳ፣ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲቀነቀን ያስቻለ ድል ነው።ኃያላኑ የምዕራብ አገራት ኤምባሲዎቻቸውን በአዲስ አበባ ከፍተው ለኢትዮጵያ ነጻና ሉዓላዊነት ‘አሜን’ ብለው ዕውቅና ሰጥተዋል።

በቅኝ ገዥዎች የአገዛዝ ፖሊሲያቸውን ጭምር እንዲመረምሩ አድርጓል። አድዋ ከድሉ ማግስት ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር መሆኗ እንዲረጋገጥ እና ድንበሯን እንድትካለልም አስችሏታል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች እንድትታወቅ፣ ዝናዋ እንዲናኝና እንድትከበር ምክንያት ሆኗል፤ ለኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት እርሾ ሆኗል። 

በዲፕሎማሲ ማዕከልነት ረገድ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ ትሆን ዘንድ አድዋ ወሳኙ እርሾ ነበር። ቅኝ ያልተገዛች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር፣ ለተቀረው አፍሪካ የነጻነት ትግል ፋና ወጊ እንድትሆን በማድረጉ ትልቅ ሚና ነበረውና!! 

አፍሪካ ሕብረት እና ፓን አፍሪካዊነት 

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በ1955 ዓ.ም በ32 ሃገራት አባልነት ተመሰረተ።

በቅርቡ በአፍሪካ ሕብረት ቅጥር ግቢ የመታሰቢያ ሃውልት የቆመላቸው (በ32ኛው የሕብረቱ መሪዎች ጉባኤ ወቅት) ቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴና ካቢኒዎቻቸው ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት ትልቅ ሚና ነው።

ሕብረቱ ንጉሰ ነገስቱ ለአፍሪካ ነፃነትና አንድነት ላደረጉት ድጋፍና ለሕብረቱ መመስረት ለተጫወቱት ሚናን ታሳቢ በማድረግ መታሰቢያ ሐውልት አቁሞላቸዋል።የአፍሪካ ሕብረት የአህጉሪቷ ሁለንተናዊ ጉዳይ የበላይ ጠባቂ ነው። የፓን አፍሪካዊነት ውጤት የሆነው ይህ ተቋም ካሉት ተልዕኮዎች መካከል አህጉራዊ ሰላም፣ ፀጥታና ደህንነት ማረጋገጥ ዕድገትና ብልጽግናን ማበረታታት ነው።

በእስካሁኑ እርምጃው ለአህጉሪቷና ሕዝቦቿ ሁለንተናዊ ደህንነትና ልማት አበርክቶቱ የሚተቸው ሕብረቱ በቅርብ ዓመታትም አፍሪካን ወደ በለጸገች አህጉር ለማሸጋገር የ2063 አጀንዳ ነድፎ ጉዞ መጀመሩ ይታወቃል።

ይህን ሕልም ዕውን ለማድረግ “የሰላምና ደህንነት መዋቅሩን በበላይነት መምራት ይገባዋል” የሚሉ ወገኖች ግን ሕብረቱ ከአፍንጫው ሥር ያለውን ክፍለ አህጉራዊ ሰላምና ደህንነት መምራት ተስኖታል በማለት ይሞግታሉ።

“ደጅ አስከባሪነቱን ተነጠቀ?” እንዴ ሲሉም ይጠይቃሉ።በአፍሪካ ጸጥታና ደህንነት ለማረጋገጥ መሪዎቹ በማህበረሰባቸው ውስጥ የፖለቲካን መነጣጠል ያጠበበ አካባቢ መፍጠር እንዳለባቸው ምሁራን ይመክራሉ።

የምርጫ ኮሚሽኖችን በራስ ፍላጎት መቀየድ፣ በፓለቲካዊ ሐሳብ ልዩነቶች ሁሉን ማግለል ለአምባገነን መሪዎች መፈጠር ምክንያት ይሆናል። እናም በአህጉሪቷ የግጭት መንስኤ የሚያጠኑ ጠንካራ ተቋማት መገንባት አካታች ዴሞክራሲያዊ ምህዳር በመፍጠር አህጉራዊ ቁልፍ ጉዳዮችን ዕልባት ከተበጀላቸው የ2063 የአህጉራዊ መዋቅራዊ ሽግግር አጀንዳ ማሳካት ይቻላል።

እናም የአፍሪካ መንግስታት ከህዝብ ጋር በተዋዋሉት ፖለቲካዊ ውል መሰረት በቅድሚያ መታደስ ያሻቸዋል። የወቅቱ ነባራዊ ሁናቴ የአፍሪካ ሕብረት ጸጥታና ደህንነቱን በበላይነት የመቆጣጠር ተስፋ ፓን አፍሪካን እንደ አካል ከመጠየቅ በላይ ይጠጥራል።

የመሪዎች ጉባዔ እና ፓን አፍሪካዊነት

 የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ "የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ማፋጠን" በሚል መሪ ሀሳብ የካቲት 11 እና 12 በአዲስ አበባ ተደርጓል። 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አማካሪ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ ስለዘንድሮው ጉባዔ በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግር ወጥታ ጉባዔውን በስኬት መስተናገዷ ብቻ ሳይሆን በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት የተፈታበት መንገድ ኢትዮጵያ አሁንም የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ የመፍታት አርዓያነቷን ያሳዬ አጋጣሚ መሆኑን ጉባኤው በአድናቆት አውስቶታል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የፖለቲካ ጉዳዮች፣ ሰላም እና ፀጥታ ዘርፍ ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ በዘንድሮው መሪዎች ጉባዔ በኢትዮጵያ ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ትልቅ አድናቆት የተቸረ እንደነበር ገልፀዋል።

 የኢትዮጵያ የሰላም ሂደት ተሞክሮ በ2063 የአፍሪካ የልማት አጀንዳ ውስጥ አንዱ በሆነው የተኩስ ድምፅ የማይሰማበት አፍሪካን ዕውን የማድረግ ግብ ማሳያ መሆኑንም እንዲሁ።

ኢትዮጵያ ተመራጭ የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን ያሳየችበት፣ በአንዳንድ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ይሰራጩ የነበሩ የተዛቡ ዘገባዎች ትክክለኛ መልክ የያዙበት እንደነበር በመግለጫው ተወስቷል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመሪዎቹ ጉባኤ የመክፈቻ ንግግራቸው ከ60 ዓመታት በፊት የአፍሪካን ትብብር ለማረጋገጥ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የመሰረቱ ቀደምት አፍሪካውያንን ራዕይ አድንቀው የአፍሪካን መፃኢ ዕድል ብሩህ ለማድረግ ከቀደምት አባቶች አንድነት መማር እንደሚያሻ የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴን ንግግር አውስተው ነበር። ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ የአህጉሪቱን ፈተናዎች በአፍሪካዊ ትብብር መቋቋምና መፍታት እንደሚቻል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ጠቅሰዋል። 

 በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ እንድታገኝ መጠየቃቸውና የዓለም አቀፉን ሚዲያ የተንሸዋረረ አተያይ ለመቀልበስ አፍሪካ አቀፍ ሚዲያ ማቋቋም እንደሚያስፈልጋት መጠቆማቸው ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነ አምባሳደር ታዬ ያነሳሉ።

ይህ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጰያ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ መገንባቷ፣ ዘንድሮም ለመጀመሪያ ጊዜ የፓን አፍሪካ ጉባዔ ማዘጋጀቷ፣ የፓን አፍሪካ ወጣቶች ጉባዔ መመስረት እንዳለበት መጠየቋም ሌላው የፓን አፍሪካዊነት መሪነቷን አሁኑም ማስቀጠሏን ማሳያ እንደሆነ አምባሳደር ታዬ ጠቅሰውታል።

 የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የፖለቲካ ጉዳዮች፣ ሰላም እና ፀጥታ ዘርፍ ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ አፍሪካ የሰላምና ፀጥታን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በመንግስታቱ ድርጅት በኩል በቂና ተመጣጣኝ የፋይናንስ ድጋፍ እንደምትሻ፣ የሰላም ማስከበር ስምሪቶች ስኬታማነት ፋይናንስና በጀት ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠውና እንደ ፀጥታ ምክር ቤት አፍሪካም የራሷ አቅሙ የጎለበተ ተቋም መገንባት እንደሚጠበቅባት፣ መፈንቀለ መንግስትን ጨምሮ ኢ-ሕገ መንግስታዊ አካሄዶችን ህብረቱ አሁንም በፅኑ እንደሚያወግዝ ጠቁመው ነበር።

 በአፍሪካ ግጭት አፈታት ሂደቶች ጥበብና ብልሃት ያላቸውን አፍሪካዊ ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉንም ህብረተሰብ ክፍል ማሳተፍ፣ አሳቢያንንና ምሁራንን ጥምረት በመፍጠር ተግባርና ንድፈ ሀሳብን በማጣጣም ውጤታማ ስራ ማከናወንና ዲፕሎማሲያዊ ስራን ማፋጠን እንደሚያም እንዲሁ።

በተመሳሳይ ከኢኮኖሚ አንጻር የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ኮሚሾነር ዶክተር አቡ ዘይድ አማኒ ደግሞ በሃይል፣ በትራንስፖርትና በዲጂታላይዜሽን ረገድ አፍሪካን እድገት ለማሳለጥ ስርዎችን አንስተዋል።

ለአብነትም በአፍሪካ ሁለንተናዊ ዕድቷን ለማረጋገጥ አፍሪካ አቀፍ አንድ የኤሌክትሪክ ኃይል ገበያ እንዲኖርም ፍኖተ ካርታ መቀረፁን፣ ለአፍሪካዊያን ትስስር ለማሳለጥ በትራንስፖርት ዘርፍም በ35 ሀገራት የአንድ የአየር ትራንስፖርት ገበያ መፈጠሩን፤ በዲጂታላይዜሽን በኩልም በሁለም መስክ አፍሪካ አቀፍ የጋራ ገበያ እንዲፋጠን የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እነዚህ ተግባራትም ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራን ለማፋጠን የሚኖራቸውን ሁነኛ አስተዋጽኦ አብራርተዋል።  በጉባዔው መዝጊያ ላይ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት እና ተመራጩ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የኮሞሮሱ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሱማኒ በሰጡት መግለጫ፤ በ2023 አፍሪካ ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ እና የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራን ቀዳሚ አጀንዳ አድርገው እንደሚሰሩ ገልጸው ነበር። 

አፍሪካ ያላት የተፈጥሮ ሀብት ማልማትና የንግድ ትስስሯን በማጠናከር ሁለንተናዊ ልማቷን ለማረጋገጥ፣ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣናውን ትግበራን ማሳለጥ፣ የአፍሪካ ድምፅ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይሰማ ዘንድ በፀጥታው ምክር ቤት አባል እንድትሆን መጎትጎትን ጠቃቅሰዋል።

አፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየሰጠ ያለው የገንዘብ ድጋፍ ኢ-ፍትሃዊነት መስተካከል እንዳለበትም የሰራ ኅላፊዎቹ በተደጋጋሚ አንስተዋል።  

አፍሪካ ለነገዋ የአድዋ ድልን ፓን አፍሪካዊነት እርሾ ብትጠቀምስ

 ኢትዮጵያ ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ቀንዲልነቷ በታሪክ መዛግብት ሰፍሯል። ለአፍሪካና ለጥቁር ሕዝቦች ታሪክና ሥልጣኔ፣ ቅርስና ባህል፣ ነጻነትና መብት ያደረገችውን ተጋድሎ ጉምቱ ፓን አፍሪካዊያኑ ይስማሙበታል።

ከደቡብ አፍሪካው የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ እስከ ኦሊቨር ታምቦና ታቦ ምቤኪ፣ ከዚሙባቡዌው ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ እስከ ሴኔጋላዊው ሴዳር ሴንጎር፣ የኬኒያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታና ሌሎችም የአፍሪካ መሪዎች ኢትዮጵያ ‘‘የአፍሪካ እናት” ሲሉ ደጋግመው ገልጸዋታል።

ኔልሰን ማንዴላ የነጻነት ረጅሙ ጉዞ (Long Walk to Freedom) በተሰኘ ግለ ታሪካቸው ‘‘ኢትዮጵያ በልቤ ውስጥ ሁልጊዜም ልዩ ቦታ አላት፤ የፈረንሳይን፣ እንግሊዝንና አሜሪካንን በጥምር ከምጎበኝ ወደ ኢትዮጵያ ሄጄ ኢትዮጵያን መጎብኘት የበለጠ ይስበኛል፣ ትልቅ ደስታንም ይሰጠኛል” ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የታሪክና የሥልጣኔ መሠረት ናት ብለው ያምናሉ። የቀድሞ የኬንያ ፕሬዚዳንት እሁሩ ኬኒያታ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢህ አህመድ በዓለ ሲመት ወቅት ‘‘ኢትዮጵያ የአፍሪካ እናት’ ብለዋታል።

የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በአንድ ወቅት በአድዋ ድል ክብረ በዓል ላይ ተገኝተው "የአድዋ መሬት የተቀደሰ ነውና ጫማዬ ላወልቅ ግድ ይለኛል" ብለው ነበር። አድዋ የአፍሪካ ቅዱስ መሬት፣ ለቅኝ ግዛት አቀንቃኞች ሃፍረት ምንጭ እንደሆነ አስረድተው ነበር።

መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ ሚድራድ ከተማ ያደረገው የፓን አፍሪካኒዝም ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፎርቹን ቻሩምቢራ ምክር ቤቱ የአፍሪካ ሕብረት የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞቾ ትግበራ መከታተልና የአፈፃፀም ክፍተቶችን መጠቆም፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታና የዴሞክራሲ ባህል ማጎልበት፣ የአፍሪካዊያን ድምፅ የሚሰማባቸውን የጋራ መድረኮች ማመቻቸትና ሀሳብ የማንሸራሸር ዕድል በመፍጠር የተሰበሰቡ ምክረ ሀሳቦችን ለሕብረቱ አስፈፃሚ አካል የማቅረብ ተልዕኮ ይዞ እንደሚሰራ ይገልጻሉ።

 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአውሮፓዊያኑ 1963 ሲቋቋም ዋናው ዓላማው ፖለቲካዊ ትብብር እንደነበር ገልፀው፣ አሁናዊ አፍሪካውያን ግን ከፖለቲካው ባለፈ በመካከላቸው ኢኮኖሚ ትስስር እንደሚያስፈልጋቸው ይጠቅሳሉ። ለዚህ ደግሞ ከቅኝ ገዥዎች አዕምሯዊ እስር ቤት ወጥተው በፖን አፍሪካዊነት እሳቤ መራመድ እንደሚገባቸው አንስተዋል።

ይሄውም የአፍሪካ ሀገራት ከቀድሞ ቅኝ ገዥዎቻቸው ጉያ ከመርመጥመጥ፣ ባህልና ኩራታቸው ከቅኝ ገዥዎቻቸው እሳቤ ከመቅዳት በበይነ አፍራካ አካሄድ፣ በፓን አፍሪካዊነት መርህ ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ ያነሳሉ።  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በፓን አፍሪካ ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ በአፍሪካ ወጣት መሪዎችን ለማፍራትና ለፓን አፍሪካዊነት መጠናከር ዐይነተኛ ሚነ እንዳለው ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያም ለፓን አፍሪካዊነት ማንሰራራት የነበራትን ታሪካዊ የመሪነት ሚና አሁንም አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠው ነበር።

ፎረሙ የፓን አፍሪካ መንፈስ እና የአፍሪካ አንድነትን እንደ አዲስ ትንሳዔው እንደሚያበስርም እንዲሁ። ሀገራት ከሰው ሰራሽ መልክዓ ምድራዊ የወሰን ሃሳብ መስመሮች፣ ከርዕዮተ ዓለም አጥሮች ወጥተው የተባበረች እና የበገለፀገች አፍሪካን ዕውን ለማድረግ አጀንዳ የሚቀርጽ፣ ተሻጋሪ ሃሳብ የሚያፈልቅ ችግር ፈች አፍሪካዊ ትውልድ መገንባት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

 የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪም የቀጣይ አፍሪካ መጻዒ ዕድልን በአድዋ ድል እርሾዎችን ተጠቅሞ መወሰን እንደሚያስፈልግ፣ የጥቁሮች አኩሪ ታሪኮችን ለትውልድ ማስተማር፣ ወጣቱን በፓን አፍሪካዊ ቅኝት መቅረጽ እንደሚያስፈልግ ይጎተጉታሉ። የአድዋ የኢትዮፐያ ትንሳዔ የአፍሪካ ትንሳኤ መሆኑን የገለጹትም ለዚህ ነው።

“ኢትዮጵያዊያን እንዳደረጉት መላ ህብረተሰቡን ካንቀሳቀስን እናሸንፋለን። ግን ምን ያህሎቻችን የተማርን ሰዎች ስለ አድዋ እና ኢትዮጵያ ታሪክ እናውቃለን። በ2004 ሃይቲ 200ኛ 'ዓመቷን የነጻነት ቀኗን አክብራ ነበር። የሃይቲ ዜጎች ከአፍሪካ በባርነት የተወሰደዱ ሰዎች ናቸው።

ሶስት ግዛተ አጼዎችን /ስርዓት መንግስታትን/ አሸንፈዋል። የብሪታኒያን፣ ስፔን እና በመጨረሻም ፈረንሳይን ሶስት ስርዓተ መግስታትን ያሸነፉ ጥቁሮች ታሪክ ነውና። ይህን ታሪክ መተረክ አለብን።

በ18ኛው ክፍል ዘመን የሃይቱ፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የአድዋና በ20ኛው ክፍለ ዘመን የደቡበ አፍሪካ አፓርታይድ ትግል የተገኙ ድሎች ታሪክ መንገር አለብን። እርስ በርስ የተሳሰሩ የአፍሪካዊያን የነጻነት ታሪኮች ናቸው።

ትልቁ እንደ አህጉር ያለብን ከፍተት እኛ አፍሪካዊያን ወጣቶች ስለራሳቸው እንዲያውቁ እና እንዲነሳሱ ማስቻል ላይ ነው። ስለራሳቸው እንድንኮራና ስለማንነታቸው ያላቸው ስሜት በማነሳሳት አፍሪካዊያን ወጣቶች አህገሪቱ ሁለንተናዊ ሽግግር እንድታመጣ ማስቻል ይገባል። አድዋ ተጠቂዎች ሳይሆን አሸናፊዎች እንደምንሆን አሳይቶናል። አድዋን መዘከር የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው" ነበር ያሉት።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም