ኢህአዴግ በጉባኤው ላሳለፋቸው ወሳኔዎች ተግባራዊነት የድርሻችንን እንወጣለን---የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢህአዴግ በጉባኤው ላሳለፋቸው ወሳኔዎች ተግባራዊነት የድርሻችንን እንወጣለን---የተለያዩ ከተሞች ነዋሪዎች
ሽሬ/ሰመራ/ነቀምት መስከረም 26/2011 ኢህአዴግ በ11ኛው ድርጅታዊ ጉበኤው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ተግባራዊ ለማድረግ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ የሽሬ እንዳስላሴ፣ የሰመራ-ሎጊያ እና የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ። በሽሬ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተስተዋለ ያለውን ሥርዓት አልበኝነት መንግስት በህግ አግባብ ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ ተናግረዋል ። ከነዋሪዎቹ መካከል መምህር በርኽ ገብረኪዳን እንደገለፁት ጉባኤው በሀገሪቱ እየታየ ያለውን ወቅታዊ የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ጉባኤው የህግ የበላይነት እንዲከበር ላሳለፈው ውሳኔ ተግባራዊነት የድርሻቸውን ይወጣሉ ። "ለተማሪዎቼ የህግ የበላይነት መረጋገጥ ያለውን ጠቀሜታ ከማስረዳት ጀምሮ ኃላፊነቴን እወጣለሁ" ብለዋል ። "የወጣቶችና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ በጉባኤው የተላለፈው ውሳኔ ስኬታማ እንዲሆን የበኩሌን ለማበርከት ዝግጁ ነኝ " ያሉት ደግሞ የከተማው የሴቶች የንግድና ዘርፍ ማህበራት ሊቀ መንበር ወይዘሮ ጥሩ ገብረሚካኤል ናቸው። በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ጀማል ዘይኑ በበኩላቸው ከአጎራባች አገሮች የተጀመረው የሰላምና አብሮ የመበልፀግ እንቅስሴ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቅጠል ድርጅቱ ያሳለፈው ውሳኔ እንደሚደግፉ ተናግረዋል ። "በተለይ ከኤርትራ ጋር የተጀመረው የሰላምና የፍቅር ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲደርስ የሚጠበቅብኝን ሁሉ እወጣለሁ" ብለዋል ። "ዜጎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር፣ የመስራትና ሀብት የማፍራት ህገ-መንግስታዊ መብታቸው ሳይሸራረፍ እውን እንዲሆን በትኩረት እንደሚሰራ በጉባኤው የተላለፈው ተገቢና ወቅታዊ ነው " ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ምጽላል ኃይሉ ናቸው፡፡ እንደ ወይዘሮ ምጽላል ገለጻ ውሳኔው በአግባቡ እንዲተገር የድርሻቸውን ይወጣሉ። በኢህአዴግ 11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ዶክተር አብይ አህመድ የግንባሩ ሊቀ መንበር ሆነው ዳግም መመረጣቸው በአገራቱ የተጀመረው የይቅርታና የፍቅር ጉዞ ይበልጥ እንዲጠናከር አስተዋፆ ያለው መሆኑን ነዋሪዎች አስታውቀዋል ። የሰመራ-ሊግያ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው በ11ኛው የኢህአዴግ መደበኛ ጉባኤ ለተላለፉ ወሳኔዎች ተፈጻሚነት የበኩላቸውን ሚና አንደሚወጡ ገልፀዋል ። ጉባኤው የድርጅቱ ዋና እና ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ የመረጣቸው ዶክተር አብይ አህመድና አቶ ደመቀ መኮንን በሀገሪቱ የተጀመረውን ተስፋ ሰጪ የለውጥ ጉዞ አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ እመነታቸው መሆኑን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል ። የሰመራ ከተማ ነዋሪ አቶ መሃመድ ሀመዲን በሰጡት አስተያየት እንዳሉት በጉባኤ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከመሰረቱ ለመፍታ በድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ የተላለፉ መልክቶችና ጉባኤው ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ተገቢና ወቅታዊ ናቸው ። በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የወሰን ችግሮችን ለመፍታትና የዜጎችን ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመሰራትና ሀብት የማፍራት መብት ለማስከበር በጉባኤው የተላለፉ ውሳኔዎች በአግባቡ እንዲተገበሩ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አቶ መሀመድ ተናግረዋል። "ለረጅም ጊዜ በአገርነት የቀጠሉት የታዳጊ ክልል መሪ ፓርቲዎችም በኢህአዴግ ስራ አሰፈጻሚ ኮሚቴና የምክር ቤት ጉባኤዎች ላይ ውክልና እንዲኖራቸው መደረጉ ጉባኤው የክልላቸው ህዝብ ጥያቄ የተመለሰበትና ታሪካዊ ወሳኔ የተላለፈበት አድረጎታል " ብለዋል ። የሎግያ ከተማ ነዋሪ አቶ እድሪስ ሰኢድ በበኩላቸው ጉባኤው "በጠላትነት ይተያዩ የነበሩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ደርጅቶች ከመገፋፋትና ከመጠላለፍ ወጥተው በአገሪቱ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በተጀመረው የለውጥ ጉዞ አብረው ለመስራት ፋላጎት ያሳዩበት በመሆኑ ታሪካዊና ልዩ ያደርገዋል " ብለዋል ። በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ የተጀመረውን ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል በእህት ድርጅቶች መካከል ወጥነት ያለው አቋም መያዙ እንዳስደሰታቸውም አቶ እንድሪስ ገልፀዋል ። በዶክተር አብይ አህመድና በቅርብ አጋሮቻቸው ግንባር ቀደም አመራርነት የተጀመረውን ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ ከዳር ለማድረስ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል ። የነቀምት ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው በአገሪቱ እየተስተዋሉ ያሉ የፀጥታ ችግሮችን በመፍታት የተጀመረውን ዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ አጠናክሮ ለማስቀጠል ጉባኤው ያሳለፈውን ውሳኔ እንደሚደግፉ ገልፀዋል ። በከተማው የቀበሌ 04 ነዋሪ አቶ ግርማ ወርቁ በሰጡት አስተያየት በ11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎች ወቅታዊና ከጊዜው ጋር የሚሄዱ ናቸው ። የተላለፉት ውሳኔዎች የሀገርቱ እድገት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ዳር ለማድረስ የሚያስችሉ በመሆናቸው ለተግባራዊነታቸው የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል ። "በጉባኤው ዶክተር አብይ አህመድና አቶ ደመቀ መኮንን በድርጅት ሊቀመንበርነትና ምክትልነት መመረጣቸው የተጀመረውን የሰላም፣ የአንድነት፣ የፍቅር፣ የመደመርና የነፃነት መርህ ለማጠናከር ያስችላቸዋል " ብለዋል ። ህብረተሰቡ ሲጠብቃቸው የነበሩ ውሳኔዎች በጉኤው መተላለፋቸው የገለፁት ደግሞ በከተማው የቀበሌ 02 ነዋሪ አቶ አማኑኤል ደበላ ናቸው ። በጉባኤው የተላለፉ ውሳኔዎች ቀጣይ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ብሩህ እንዲሆን ሚናቸው የጎላ በመሆኑ ለተፈጻሚነታቸው የድርሻቸውን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።