ቀጥታ፡

የዚህ ዘመን ትውልድ ታሪክን ከአድዋ በመማር የራሱን በጎ አሻራ ለማሳረፍ መትጋት አለበት - የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

ጅማ የካቲት 22/2015(ኢዜአ) የዚህ ዘመን ትውልድ አንድነትን፣ እኩልነትንና መተባበርን ከአድዋ በመማር የራሱን በጎ አሻራ ለማሳረፍ መትጋት አለበት ሲሉ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

 አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን መካከል ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ከተቦ አብዲዮእንዳሉት የአድዋ ድል “ከመለያየት ይልቅ አንድነት፣ አሸናፊነትና ጀግንነት መሆኑን ያየንበት አኩሪና አስተማሪ ታሪካችን ነው”። 

በዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ከተቦ እንዳሉት "አድዋ ጥቁሮች ስለ ነጻነታቸው ቀና ብለው ማውራት እንኳን በማይችሉበት ዘመን "ኢትዮጵያ ለጥቁር ሕዝቦች ብርታት የሆነ ድል ያስመዘገበችበት እለት ነው" ይላሉ።

 በዘመኑ ኢትዮጵያውያን ለነጻነታቸውና ለክብራቸው ሲሉ መከፈል የሚገባውን መስዋዕትነት ሁሉ የከፈሉበት ጊዜ መሆኑንም ገልጸዋል። 

አድዋ የሉአላዊነታችን መሰረት፣ የአንድነታችን ምልክት እና ለነጻነታችን ያደረግነው የትግል አርማችን ስለመሆኑ ብዙዎች የሚመሰክሩት የታሪክ ሀቅ በመሆኑ በኩራት የሚዘከር ታሪካዊ ቀን መሆኑንም አንስተዋል። 

ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ እንደማይደራደሩ እና ከምንም በላይ ለነጻነታቸውና ለሀገራቸው የሚሰጡትን የላቀ ክብር ነው ብለዋል፡፡ 

ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ካሉበት አካባቢዎች ሁሉ ሄደው በደማቸውና በአጥንታቸው የአንጸባራቂው ድል ተሳታፊዎች አንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡

 በአድዋ ጦርነት ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ተሳታፊ የሆኑበትና አንድነት የታየበት ጊዜ በመሆኑ ያንን ስናከብር የአሁኑ ትውልድ የራሱን አድዋ በተግባር በመስራት ነው ብለዋል፡፡ 

በተለይም በዚህ ዘመን ትውልዱ ከአድዋ ሊማር የሚገባው በርካታ ቁምነገሮች መኖራቸውን የገለጹት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፤ አንድነትን፣ እኩልነትን፣ መተባበርን ከአድዋ ታሪክ መማርና በራሱ ቁምነገር ሰርቶ ማለፍ ይገባል ብለዋል፡፡ 

ይህ በዓለም ላይ ጉልህ እና ግዙፍ የነጻነት ድል የመላው ኢትዮጵያውያን የአንድነት ድል በመሆኑ ትብብር ምን ያህል አቅምና ሃይል የሚፈጥር ስለመሆኑ መረዳት ይገባናል ብለዋል፡፡  

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ተመስገን ለሜሳ በበኩላቸው ''አድዋ ሀገራችን የነጻነት ምልክት እንድትሆን ያደረገ፣ የሁላችንም አኩሪ ታሪክ ነው'' ብለዋል።

 ''ኢትዮጵያውያን ድላችንን እየዘከርን እኛም የሚጠበቅብንና በተተኪው ትውልድ የሚታወስ ታሪክ ሰርተን ማለፍ ይኖርብናል'' ነው ያሉት።

 ረዳት ፕሮፌሰሩ አክለውም ለአድዋ ድል መላው ኢትዮጵያውያን በትብብርና በአንድነት ያስመዘገቡት ድል በመሆኑ የአሁኑ ትውልድም ተጋግዞ እና ተስማምቶ መታወስ የሚችል አዎንታዊ ስራ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

 ጥንት አባቶቻችን ለሀገራቸው አንድነትና ለነጻነቷ የነበራቸው ቀናኢ አመለካከት ለአድዋ ድል እንዳበቃቸው የሚገልጹት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ትውልዱ ከታሪክ ተምሮ ሀገሩን በተሻለ ሁኔታ የሚያስቀጥል መሆን አለበት ብለዋል። 

''ዛሬም ታግለን ድል መንሳት የሚገባን በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ያሉብን በመሆኑ እነሱን አሸንፈን የአድዋን ታሪክ በሌላ ገጽታ መድገም እንችላለን'' ነው ያሉት። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም