ቀጥታ፡

የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብርን ከግብርና ምርታማነትና የገበያ ትስስር ጋር በማቀናጀት ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ ይገባል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 22/2015 በአፍሪካ ያለውን አገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ከግብርና ምርታማነትና የገበያ ትስስር ጋር በማቀናጀት ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባ ተጠቆመ።

8ኛው የአፍሪካ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ቀን በአዲስ አበባ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ በውይይት ተከብሯል።

በመድረኩም የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንዲሁም ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የመጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

መድረኩም በዋናነት የአፍሪካ አገራት በአገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ያላቸውን ልምድ የሚለዋወጡበት ከመሆኑም ባሻገር በአገራቱ መካከል ቅንጅታዊ አሰራር ለማዳበር እንደሚያግዝ ነው የተገለጸው፡፡

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ህብረት የትምህርት፣ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኮሚሽነር መሃመድ ቤልሆሲን እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ 66 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት የአገር በቀል የትምህርት ቤት ምግባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

መርሃ ግብሩ ከትምህርት ዘርፍ ባሻገር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰው፤ በዚህም ሰላማዊና የበለጸገች አፍሪካን ለመፍጠር የሚከናወኑ ሥራዎች አካል ተደርጎ እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።

መርሃ ግብሩ በግብርና፣ በሥርዓተ-ምግብና በሌሎች ዘርፎች የእሴት ሰንሰለት በመፍጠር ዘላቂ ልማት እውን ለማድረግ እንደሚያግዝም ነው ያብራሩት።

የዓለም የምግብ መርሃ ግብር የትምህርት ቤት ምገባ ዳይሬክተር ካርሜን ባርባኖ በበኩላቸው በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የአፍሪካ አገራት ለጉዳዩ የሰጡት ትኩረት የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

እነዚህ አገራት ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ገደማ ለትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር የሚሰጡትን የፋይናንስ ድጋፍ በ15 በመቶ እንደጨመሩ በመጠቆም።

በዚህ ረገድ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት አብነት የሚሆን ሥራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በየዓመት ከአገሪቱ በጀት ውስጥ 85 ሚሊዮን ዶላር ለአገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር እንደሚበጅት ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ መንግሥት ለትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

ለአብነትም በአዲስ አበባ መርሃ ግብሩ በሙከራ ደራጃ በ2011 ዓ.ም እንደተጀመረ አስታውሰው፤ አሁን ላይ በመዲናዋ 700 ሺህ ገደማ ተማሪዎች የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

መርሃ ግብሩ ተማሪዎች ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር ለበርካታ እናቶች የሥራ እድል መፍጠሩንና የገበያ ትስስር በማጎልበት ረገድም በጎ ሚና እያበረከተ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

መርሃ ግብሩ ወደ ትምህርት ገበታ የሚሄዱ ህጻናትን ከመጨመሩ በላይ ከትምህርት ገበታ የመቅረት ምጣኔ እንዲቀንስ አድርጓል ነው ያሉት፡፡

የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር የተማሪዎችን ሥርዓተ ምግብና ጤና በማሻሻል የመማር ብቃታቸው እንዲጨምር እንደሚያደርግ የተናገሩት ደግሞ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ናቸው፡፡

በተጨማሪም መርሃ ግብሩ በግብርና ምርት እሴት ሰንሰለት አማካኝነት አርሶ አደሮችን፣ የአርሶ አደር ማህበራትን እንዲሁም የምግብ ማቀነባበር ኢንዱስትሪዎችን እንደሚጠቅም አብራርተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያ በ10 ዓመቱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ውስጥ የትምህርት ዘርፍ ልማት እቅድ አካል ተደርጎ እየተተገበረ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም