የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ተፈናቃይ ወገኖችን መልሶ የማቋቋም ፕሮጀክት አስጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ተፈናቃይ ወገኖችን መልሶ የማቋቋም ፕሮጀክት አስጀመረ
አሶሳ(ኢዜአ) የካቲት 22 / 2015 የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቃይ ወገኖችን መልሶ የማቋቋም ፕሮጀክት አስጀመረ::
ፕሮጀክቱን ስኬታማ ለማድረግ ያለመ ውይይት ዛሬ በአሶሳ ከተማ እየተካሄደ ነው::
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የአደጋ ስጋት ቁጥጥር ክፍል ኃላፊ አቶ ድረስ ደስይበለው በወቅቱ እንዳሉት ፕሮጀክቱ በክልሉ በጸጥታ ችግር ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖችን መልሶ ማቋቋም ላይ ያተኮረ ነው::
"በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የሚተገበረው ፕሮጀክት ወደ ቀያቸው የተመለሱ 640 አባወራዎችን ከጊዜያዊ ወደ ቋሚ መጠለያ እንዲሸጋገሩ ያደርጋል" ብለዋል::
በፕሮጀክቱ ለተፈናቃይ ወገኖች ንጹህ መጠጥ ውሃ በማቅረብ ከተላላፊ በሽታዎች እንዲጠበቁ ማድረግን ጨምሮ በጥቃቅንና አነስተኛ ስራዎች በመሳተፍ በሚያገኙት ገቢ በዘላቂነት ራሳቸውን እንዲችሉ የማገዝ ተግባት እንደሚከናወኑ ጠቅሰዋል ።
ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የሚውለው ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ከጀርመን ቀይ መስቀል ማህበር በድጋፍ መገኘቱን ሀላፊው አስታውቀዋል::
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ሞገስ ነገሮ ፕሮጀክቱ በክልሉ መንግስት የሚያከናውነውን መልሶ ማቋቋም በማገዝ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እንደሚያጠናክር ገልጸዋል::
የጀርመን ቀይ መስቀል ፕሮግራም ተወካይ ሚስተር ክሊፍ ሙሻያ ማህበራቸው ለፕሮጀክቱ አፈጻጸም ስኬት የቅርንጫፉ ሠራተኞችን አቅም ለማጎልበት ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል::