ቀጥታ፡

ወጣቱ የአባቶቹን የጀግንነት፣ የአንድነትና የአሸናፊነት ታሪክ በማጽናት ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ

ጋምቤላ (ኢዜአ) የካቲት 22/2015 ''ወጣቱ ትውልድ የአባቶቹን የጀግንነት፣ የአንድነት እና የአሸናፊነት ታሪክ በማጽናት ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል" ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ።

ርዕሰ መስተዳድሩ 127ኛው የአድዋ ድል በዓል በማስመልከት ለክልሉና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳቹሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አቶ ኡሞድ በእዚሁ ጊዜ እንዳሉት ጀግኖች አባቶች በአድዋ ጦርነት የውጪ ወራሪን በድል አድራጊነት ያሸነፉት በጀግንነታቸው፣ በአንድነታቸውና በዓላማ ጽናታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ወጣቱ ትውልድ እነዚህን የአባቶቹን እሴቶች በማጽናት በክልሉ ብሎም እንደሀገር ዘላቂ ልማትና ብልጽግ ለማምጣት ጠንክሮ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።

ጀግኖች አባቶች የውጪ ወራሪን አሳፍረው በመመለስ የኢትዮጵያን ክብርና ነፃነት እንዳስጠበቁ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም ህብረ ብሔራዊ አንድነቱን በማጠናከር ሀገርን ከድህነት ነፃ ለማውጣት በጽናት እንዲሰራ አሳስበዋል።

የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ጽናትን፣ በዘመን የማይሸረሸር ጀግንነትን፣ ክብርን፣ ነፃነት፣ አንድነትንና መሰል ቱሩፋቶችን ያጸና ደማቅ ታሪክ መሆኑንም ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመጨረሻም ለክልሉ እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ 127ኛው የአድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳቹ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘንድሮ "አድዋ: አንድነት፣ ጀግንነትና ጽናት" በሚል የሚከበረው 127ኛው የዓድዋ ድል በዓል በክልሉ በፓናል ውይይት እንዲሁም በወታደራዊና ባህላዊ የሰልፍ ትርኢት በድምቀት እንደሚከበር ከበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም