ቀጥታ፡

አዲሱ ትውልድ የአድዋ ድል ተሞክሮን በመቀመር በሁሉም መስኮች የበለፀገች ኢትዮጵያን መገንባት ይገባዋል- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 22/2015 አዲሱ ትውልድ የአድዋ ድል ተሞክሮን በመቀመር በሁሉም መስኮች ያደገች እና የታፈረች ኢትዮጵያን መገንባት እንደሚጠበቅበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ።

 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት ሰራተኞችና አመራሮች 127 ኛውን የአድዋ ድል በዓል በድምቀት አክብረዋል። 

በዓሉን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፤ የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን መላው ጥቁር ሕዝብ የሚኮራበት ታሪክ ነው ብለዋል።

 ድሉ ለአገራቸው ነጻነት ቀናኢ የሆኑ፤ የአይደፈሬነት የመንፈስ ጽናት ያላቸው ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ደማቅ ተጋድሎ መሆኑን ነው የተናገሩት።

 የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ከሁሉም አቅጣጫ በአንድ ልብ መክረው ጠላትን ድል የነሱበት የአገራቸውን ነጻነት እና ክብር ለቅኝ ገዥዎች አሳልፈው ላለመስጠት መስዋዕትነት የከፈሉበት መሆኑን ጠቁመዋል። 

የአድዋ ድል ሲከበር መዘከር ያለበት ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ነጻነትና ክብር ያላቸው ጽኑ አቋም ከብረት የጠነከረ መሆኑን በማመላከት ነው ብለዋል። 

ጥንት እናቶቻችን እና አባቶቻችን ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ምልክት እንድትሆን ካደረጉበት የአንድነት እና የመተባበር ጥበብ ብዙ ትምህርት መቅሰም ይገባናል ብለዋል። 

የአድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው ጥቁር ሕዝብ የመንፈስ ብርታት የሆነ፤በቅኝ ግዛት ቀንበር ይማቅቁ ለነበሩ አገሮች ነፃ የመውጣትን የብርሃን ጮራን የፈነጠቀ መሆኑን አንስተዋል። 

በዓሉ ሲከበር የቀደምት ወላጆቻችን ተጋድሎ መዘከር ብቻ ሳይሆን ከአድዋ ድል ምን እንማራለን የሚለውን ጉዳይ የሚያነሳ ሊሆን እንደሚገባም ተናግረዋል።

 የአሁኑ ትውልድ ከአድዋ ድል አያሌ ቁም ነገሮችን መቅሰም እንደሚችል ገልጸው ከነሱ ጀግንነት ድህነትን ማሸነፍ የሚችልበት መንገድን ሊማር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

 ለአብነትም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀቶችን በፍጥነት የማጠናቀቅ ስራ አንዱ ጀግንነት ሊሆን እንደሚገባም በአጽንኦት ገልጸዋል። 

በመጨረሻም በማህበረሰቡ መካከል ልዩነቶችን ብቻ ሳይሆን ወደ ፅኑ አንድነት ሊወስዱ የሚችሉ ሰበዞች ላይ ማተኮር እንደሚገባም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም