በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ የተመራ ልዑክ ቦረና ዞን ያቤሎ ከተማ ገባ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ የተመራ ልዑክ ቦረና ዞን ያቤሎ ከተማ ገባ
የካቲት 22/2015 (ኢዜአ) የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ የተመራ ልዑክ ቦረና ዞን ያቤሎ ከተማ ገባ።
የልዑካን ቡድኑም የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አወሉ አብዲ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሃመድ፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋና የኢፌዴሪ አየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳን የያዘ ነው።
ልዑኩ በቆይታው በድርቁ ሳቢያ የተጎዱ ወገኖችን የሚጎበኙ ሲሆን የተለያዩ የመሰረተ ልማቶችንም ይጎበኛሉ ተብሏል።
በተጨማሪም ከቦረና ዞን ነዋሪዎች ጋር ውይይት እንደሚያካሂዱም ይጠበቃል።
በቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለጉዳት መዳረጋቸው ይታወቃል።
በርካታ እንስሳትም በድርቁ ሳቢያ የሞቱ ሲሆን ሌሎችም አስቸኳይ ድጋፍ ካላገኙ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸው ተገልጿል።
በድርቅ የተጎዱትን የቦረና ዞን ነዋሪዎች ለመታደግ መንግስት ተከታታይ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የግድብ ግንባታዎችን ጨምሮ የተለያዩ የውሃ ፕሮጀክቶች ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚከናወኑ ተገልጿል።