ቀጥታ፡

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ

አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 22/2015 ተራዝመው የነበሩ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ።

ጨዋታዎቹ የተራዘሙት በድሬዳዋ በጣለው ከባድ ዝናብ ሜዳው ማጫወት ባለመቻሉ ምክንያት ነው።

የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር የውድድር እና ስነ ስርዓት ኮሚቴ ጨዋታዎቹ ዛሬ እንዲካሄዱ መወሰኑ ይታወቃል።

በዚሁ መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድሬዳዋ ከተማ በድሬዳዋ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ29 ነጥብ ሁለተኛ እንዲሁም ድሬዳዋ ከተማ በ18 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ የፕሪሚየር ሊጉን መሪነት ከኢትዮጵያ መድን ይረከባል።

በሌላኛው የ15ኛ ሳምንት መርሐግብር ባህር ዳር ከተማ ከወላይታ ዲቻ ከምሽቱ 1 ሰአት ይጫወታሉ።

ባህር ዳር ከተማ በደረጃ ሰንጠረዡ በ26 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ተቀምጧል። ወላይታ ዲቻ በ20 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ከሁለቱ ጨዋታዎች በኋላ የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር ይጠናቀቃል።

የሁለተኛ ዙር የሊጉ ውድድር ደግሞ ነገ ይጀመራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም