ከአድዋ ድል የወረስነውን አንድነትና የሀገር ፍቅር በመላበስ ኢትዮጵያን ለመገንባት እንተጋለን - የአምቦ ከተማ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ከአድዋ ድል የወረስነውን አንድነትና የሀገር ፍቅር በመላበስ ኢትዮጵያን ለመገንባት እንተጋለን - የአምቦ ከተማ ወጣቶች
አምቦ(ኢዜአ) የካቲት 21/2015 --''ከአድዋ ድል የወረስነውን አንድነትና የሀገር ፍቅር በመላበስ ኢትዮጵያን ለመገንባት እንተጋለን'' ሲሉ የአምቦ ከተማ ወጣቶች ተናገሩ፡፡
''ቀደምት አባቶቻችን ወራሪ ጦርን አድዋ ላይ ድል በመንሳት ያስረከቡንን ሀገር ለመጠበቅ ዝግጁ ነን ሲሉም'' ወጣቶቹ ተናግረዋል፡፡
ለኢዜአ አስትያየታቸውን ከሰጡ የአምቦ ከተማ ወጣቶች መካከል መረራ ደጉ “አባቶች በከፈሉት መስእዋትነት የተገኘው የአድዋ ድልን እንደ አርዓያ በመውሰድ ኢትዮጵያን ለመገንባት የድርሻችንን እንወጣለን'' ብሏል።
''በዛ ዘመን የኢትዮጵያ አባቶች ተባብረው በመነሳት ጠላትን ድል አድረገው ዛሬ በዓለም ህዝብ ፊት በሙሉ ክብር መቆም የሚያስችል ታሪክ እንዲኖረን አድርገዋል'' ነው ያለው።
በዚህ ዘመንም አባት አርበኞች ጠብቀው ያቆዩትን ሀገር ለማስቀጠል ከእያንዳንዱ ወጣት የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።
የህዝብ አንድነትን የሚጻረሩ አመለካከቶችና አስተሳሰቦች እንዲወገዱና የሀገር ሉአላዊነት እንዲጠበቅ የበኩሉን እንደሚወጣም አስገንዝቧል።
''የጥንት አባቶች በከፈሉት መስእዋትነት የተገኘው የአድዋ ድል ከሀገር አልፎ ለአፍሪካም የትግል ተምሳሌት የሆነ ነበር” ያለው ደግሞ ወርቅነህ ሁንዴሳ ነው፡፡
አድዋ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ድል ከመሆኑ ባለፈ የኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊነት ጎልቶ የተንጸባረቀበት እንደነበረም አስታውሷል፡፡
“በዚህ ዘመንም ከአድዋ ድል የወረስነውን የህዝቦች አንድነትና የሀገር ፍቅር ስሜት በመላበስ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የድርሻችንን እንወጣለን'' ብሏል፡፡
አድዋ የኢትዮጵያ ድል ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካዊያን ጭምር ኩራት የሆነ የድል ቀን በመሆኑ የዚህ ዘመን ወጣትም ሊዘክረው ይገባል ሲልም አክሏል፡፡
ወጣቱ ድሉን ጠብቆ ከማቆየት ባሻገር የሀገሩን ታሪክ፣ ባህልና ወግ በመገንዘብ ከድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅ ሊተጋ እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡
ሌላው ወጣት ደቻሳ ለበታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወጣት የአድዋን መንፈስ በመላበስ ሀገሪቷን ለመከፋፈልና ለመበታተን የሚሰሩ ቡድኖችን መመከት አለበት ብሏል።
የአድዋ ድል በተለያየ የሙያ መስክና የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው አንድ ሆነው ድል ያስመዘገቡት አኩሪ ታሪክ ስለሆነ ሁሉም ዜጋ የአድዋን ድል ታሪኮችና እሴቶች መጠበቅና መንከባከብ እንዳለበትም መክሯል።
ጀግኖች አባቶችና እናቶች በአድዋ ጦርነት በከፈሉት ድል ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስረከባቸውን ገልጾ ''እኛም ከምንም በላይ ኢትዮጵያን ማስቀደም ይጠበቅብናል'' ብሏል፡፡
የአድዋ ድል ትውልድን ከትውልድ የሚያስተሳስር ታሪካዊ ድል መሆኑንና ድሉ የመላው ኢትዮጵያዊያን አንድነት የታየበት እንደነበር በሁሉም ዘንድ የጋራ ግንዛቤ ሊያዝ እንድሚገባም ተናግሯል።
''የቀድሞ አባቶቻችን ወራሪ ሀይልን በአድዋ ላይ ድል በመንሳት ያስረከቡንን ሀገር ለመጠበቅ ዝግጁ ነኝ'' የሚለው ደግሞ ወጣት ኬንቦኒ ዲሪባ ነው፡፡
''ኢትዮጵያውያን አባቶች ተባብረው በከፈሉት መሰዋዕትነት በዓለም ፊት በኩራት እንድንቆም ያደረገን ነው'' ብሏል።
127ኛው የአድዋ ድል በዓል የፊታችን ሀሙስ የካቲት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።