በሐረሪ ክልል ሕዝብን ለምሬት እየዳረጉ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አስፈጻሚ አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል -የምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል ሕዝብን ለምሬት እየዳረጉ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አስፈጻሚ አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል -የምክር ቤት አባላት
ሐረር ፤ የካቲት 21 ቀን 2015(ኢዜአ) ፡- በሐረሪ ክልል ሕዝብን ለምሬት እና ቅሬታ እየዳረጉ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አስፈጻሚ አካላት በተለየ ትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት ቤት አባላት አሳሰቡ፡፡
ምክር ቤቱ ለሁለት ቀናት ሲያካሄድ የቆየው ስድስተኛ ዙር ሁለተኛ ዓመት ሶስተኛ ዙር መደበኛ ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።
የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሕገ ወጥ አሰራር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶች የምክር ቤቱ አባላት ካነሷቸው ሀሳቦች መካከል ይገኙበታል።
የምክር ቤቱ አባል አቶ ዱላ ማኖጂ ፤ በሐረሪ ክልል አንዳንድ ወረዳዎች ሕገወጥ ደረሰኝ በማሳተም ገቢ የሚሰበሰብበት ሁኔታ መኖሩ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተገናኘ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር ትከረት እንደሚያሻው አንስተዋል፡፡
“የተቋሙ ሰራተኞች ብቃት ማነስና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ሕዝብን ለምሬት እያዳረገ እንደሚገኝ እና አስፈጻሚው አካል የማስተካከያ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል።
ሌላኛው የምክር ቤቱ አባል አቶ ጂብሪል መሐመድ በበኩላቸው፤ በክልሉ ሕገወጥ የነዳጅ ግብይት በጎዳናዎች ላይ በግልፅ እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በሕገወጥ መንገድ ነዳጅ በሚሸጡ ማደያዎች ላይ አስፈጻሚ አካል ተከታትሎ እርምጃ በመውሰድ ስርዓት የማስያዝ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት ለማህበረሰቡ በቂ ውሃ ማቅረብ እንዳልተቻለ የገለጹት ደግሞ የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ረምዚያ አብዱልዋሲ ናቸው።
በክልሉ አብዛኛውን ማህበረሰብ የጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ቢቻልም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መጉላላቶች በመኖራቸው የእርምት እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው፤ ከድሬዳዋ አሰን ሊሶ ገጠር ቀበሌ የሚመጣው የንጹህ መጠጥ ውሃ በኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ምክንያት ችግር በማጋጠሙ በክልሉ ገጠር እና ከተማ በቂ ውሃ ማቅረብ አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡
ችግሩን ለማቃለል ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
በከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታትም በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ ቅድመ ዝግጅት ሳይኖር በጀት የሚለቀቅላቸው ፕሮጀክቶች ክልሉን ለኪሳራ እየዳረጉ መሆናቸውንም ርዕሰ መስተዳድሩ በማብራሪያቸው አንስተዋል።
የቅድመ ዝግጅት ስራ አለመኖር እና የካሳ ጥያቄ በዘርፉ እየተስተዋሉ የሚገኙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቁመው ፕሮጀክት አስፈቅደውና በጀት ተለቆላቸው ወደ ስራ ያልገቡ አመራሮች በሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል።