ቀጥታ፡

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲዳማ ቡና ከወራጅ ቀጠና የወጣበትን ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል

አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 21/2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ15ኛ ሳምንት ጨዋታ ሲዳማ ቡና ኢትዮ ኤሌትሪክን 1 ለ 0 በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አሳክቷል።

በድሬዳዋ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የአጥቂ መስመር ተሰላፊው ሳላዲን ሰኢድ በ51ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ሲዳማ ቡናን አሸናፊ አድርጓል።

ውጤቱንም ተከትሎ ሲዳማ ቡና ነጥቡን ወደ 19ኝ በማሳደግ ከነበረበት 14ኛ ወደ 11ኛ ደረጃ ከፍ በማለት ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ችሏል።

በአንጻሩ ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌትሪክ በስምንት ነጥብ በነበረበት 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የካቲት 18 ቀን 2015 ዓ.ም በድሬዳዋ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት 18ኛው ደቂቃ ላይ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን ዛሬ ጨዋታው የቀጠለው ከቆመበት ደቂቃ ጀምሮ ነው።


በሌላኛው የ15ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐግብር ኢትዮጵያ ቡና ከፋሲል ከነማ በድሬዳዋ ስታዲየም ጨዋታቸውን በማድረግ ላይ ናቸው።


የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በድሬዳዋ በጣለው ዝናብ ሜዳው ማጫወት ባለመቻሉ ወደ ዛሬ የተራዘመ ጨዋታ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም