በመዲናዋ የምገባ መርሐ-ግብር አቅመ ደካሞችን የመደገፉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የምገባ መርሐ-ግብር አቅመ ደካሞችን የመደገፉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 21/2015 በአዲስ አበባ ከተማ የምገባ መርሐ-ግብር አቅመ ደካሞችን የመደገፉ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ዳይሬክተር ካርመን ባርበን፣ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የትምህርት ሚንስትሮችና የዓለም ምግብ ፕሮግራም አመራሮች በመዲናዋ የሚገኙ የምገባ ፕሮግራም ማዕከላትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ጉብኝቱ ስምንተኛውን የአፍሪካ የትምህርት ቤት ምገባ ቀንን በማስመልከት የተደረገ መሆኑም ተገልጿል።
በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት የምገባ መርሃ ግብሩ በርካታ ውጤቶች አስገኝቷል።
የምግባ መርሃ ግብሩ ከራስ አልፎ ለአፍሪካም መልካም ተሞክሮ መሆን ችሏል ያሉት ከንቲባዋ ባለኃብቶችን፣ ወጣቶችን እንዲሁም ባለድርሻ አካላትን በማቀናጀት በፕሮግራሙ የበርካቶችን ሕይወት መቀየር መቻሉን ገልጸዋል።
በምገባ መርሐ--ግብሩ አቅመ ደካሞችን የመደገፍ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ዳይሬክተር ካርመን ባርበን የአዲስ አበበ የምገባ ምርሐ-ግብር የሚበረታታ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
መርሐ ግብሩ ከመንግሥት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸው በአገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ቤት ምገባ እንዲጠናከር አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በምገባ ፕሮግራም ሊለካ የሚችል ውጤት አይተናል ያሉት ደግሞ በዓለም የምግብ ፕሮግራም የአፍሪካ ኅብረት ተጠሪ ዶክተር ሀሚድ ኑሩ ናቸው።
አክለውም ተፈጻሚ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ቁርጠኛ ሆነው በመሥራታቸው የተገኘ ውጤት ነው ሲሉ አተያየታቸውን ሰጥተዋል።