ቀጥታ፡

የካቲት - የድልና ገድል ወር

(አየለ ያረጋል)

በየክፍላተ-ዓለሙ ዓመታት በወራት ሲመነዘሩ የራሳቸው መልክና መገለጫ ይኖራቸዋል። እንደየንፍቀ ክበቡ ወቅቶች የራሳቸው ጸባይ፣ ክዋኔ፣ ትውስታና ትዕምርት ይቸራቸዋል።

ኢትዮጵያ ብቸኛዋ ባለ13 ወር ጸጋ ናት። ከጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ቀመርም ሰባት ዓመት ከስምንት ወራት ልዩነት አላት። በባሕር ሃሳብ ምሁራን የኢትዮጵያን ወቅቶች መጸው(መኸር)፣ ሐጋይ(በጋ)፣ ፀደይ(በልግ) እና ክረምት በሚል አራት ወቅቶችና አውራኅ ይከፍሉታል።

ሁሉም አውራኅ፣ እያንዳንዱ ወራት በራሳቸው ተፈጥሯዊና ባህላዊ ቀለማትን ይጎናጸፋሉ። የወራቱ ቅላሜና ሕብርነት ልዩ መልክዓ-ኢትዮጵያን ይፈጥራል። ከዘመን መባቻው መስከረም እስከ ማዕዶተ-ዘመኗ ጳጉሜን ወራቱ በሰማይና በምድሩ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ውቅራቸው ግላዊ ገጽታ ይነበብባቸዋል።

የኢትዮጵያ ወራት ስያሜ ከመልክና ግብራቸው ይመነጫል። እናም አገር በወራት፣ ወራትም በቀለማት ይገለጻሉ። ከባህላዊና ተፈጥሯዊ መልክና ውቅራቸው ባሻገር ግን ስምና ግብራቸው የሚጣጣሙም አሉ። አንዳንድ ወራትና ቀናት የአገራትን ዕጣ ፈንታ ይወስናሉ፤ ታሪክ ይቀይራሉ፤ ዘመን ተሻጋሪ አሻራ አሳርፈው ሲያልፉ በትውልድ ይዘከራሉ።

ከሁሉም ወራት ግን ከታሪካዊ ሁነቶች አንጻር የካቲት ልዩ ገጽታ አለው። አሁን ወቅቱ በጋ ወይም ሐጋይ ነው። ሐጋይ ከታኅሣሥ 26 እስከ መጋቢት 25 ሦስት የበጋ ወራትን ይሸፍናል። ወርኅ የካቲትንም የሐጋይ አውራኅ ደማቁ ገጽ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ውስጥ ወርኅ የካቲትን ያክል በየታሪክ ህዳጉ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ የወሰነ ወቅት ያለ አይመስልም።

የካቲት የበጋ ወርኅ አልፎ የበልግ ጊዜ መግቢያ ነውና የቋንቋ ሊቃውንቱ 'የካቲት'ን ስያሜ 'የመከር ጫፍ መካተቻ፤ የበልግ መባቻ " ይሉታል። የመኸር ምርት የሚከተትበት ነው። በኢትዮጵያ ዘመን ስሌትም መንፈቅ ዓመት ወይም ስድስተኛው ወር ነው።

ወርኅ የካቲት በመካከለኛው ዘመን ዝነኛውን ንጉስ አፄ ሠርፀድንግልን፣ የአድያምሰገድ ኢያሱን ልጅ ዳግማዊ አፄ ዳዊት(አድባር ሰገድን)፣ “የዘመናዊት ኢትዮጵያ ጠንሳሽ ናቸው” የሚባሉትን አፄ ቴዎድሮስንና ንግስት ዘውዲቱን አንግሷል።

ከጦረኞቹም ግራኝ አህመድን፣ አፄ ሚናስን፣ እቴጌ ጣይቱን፣ እቴጌ መነንን፣ ንጉስ ወልደጊዮርጊስን፣ ራስ ደስታ ዳምጠውን፣ ራስ አሉላ እንግዳን እና ሌሎች የዓድዋ ብሔራዊ የጦር ጀግኖችን አሳርፏል።

በሌላ በኩል በኪነ-ጥበብ መስክ ደግሞ ወርኅ የካቲትን ያህል የሞት ዶፍ የወረደበት ወቅት እንደሌለ ብዙዎቹ ይስማማሉ። ለአብነትም ሞገደኛው ብዕረኛ አቤ ጉበኛ እረፍት የካቲት 2፣ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር የካቲት 12፣ ጸጋዬ ገብረመድህን የካቲት 18፣ ማሞ ውድነህ የካቲት 23፣ እንዲሁም ተወዳጁ ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ እንደወጣ የቀረው የካቲት 24 ነበር። የካቲት በርካታ የምንኮራባቸው ሰዎች የተወለዱበትና በሞት ያጣንበትም ወር ነው።

የካቲት ታላቅ የሰማዕትነት ወር ነው፤ በ1929 ዓ.ም 30 ሺህ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በጅምላ በአካፋና በዶማ በግፍ የተጨፈጨፉት በወርኅ የካቲት ነው።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የጣሊያን ወራሪን በማሳፈር ለጥቁር ሕዝቦች ቀንዲል የሆነውን የዓድዋ ድል የተቀዳጀችው በየካቲት መገባደጃ ወቅት ነበር። ከነገ በስትያ ለ127ኛ ጊዜ የሚከበረው መልከ-ብዙው ዓድዋ ድል፤ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ተከውኗል።

በዚያች ተዓምረኛ ዕለት በዓድዋ ተራሮች መንደር መድፎች አጓርተዋል፤ መትረየሶች አሽካክተዋል፤ እሳት ወርዷል፤ ጥይት ዘንቧል፤ ጎራዴ ተመዟል፤ ጦር ተሰብቋል። በጥቅሉ የክቡር ሰብዓ ዘሮች ደም ተገብሯል።

የዓድዋ ድል ህያውነት፣ እንቆቅልሽነት፣ አድማስ ዘለል ታሪክነት፣ የዓለም ነፀብራቅነት፣ አፍሪቃዊነት፣ ኢትዮጵያዊነት ተዘርዝሮ አያልቅም፤ በዓድዋ ጦርነት የተመዘገቡ የይቅርታ፣ የፍቅርና የርህራሄ እሴቶች ከጥቁር ሕዝቦች ድልነት አሻግረው ለእያንዳንዱ ሰው ድል አድርገውታል።

ዶክተር ተሻገር ሽፈራው ‘የነፍስ ርችቶች’ በተሰኘችው የግጥም ስብስብ መጽሐፉ ከቋጠራቸው ስንኞች መካከልም በዓድዋ 100ኛ ዓመት ክብረ በዓል የግጥም ውድድር ያሸነፈበት ረዥምና ድንቅ ግጥሙ ነው። ከዚህ ግጥም ስንኞች መዘን ብንመለከት ገጣሚው ዓድዋ የአፍሪካዊያን ሁሉን አቀፍ ድል ለመግለጽ የቀለም፣ የአንደበት ብራና ወኔ እንዳጣባት ገልጾ፤ ለዓድዋ መጮኽና መዘከር እንደሚገባ ያነበንባል።

(…)

የታሪክ ፋኖ ዱካው – ሁሉን ችሎ መች ሊያተርፈው

በምን ቀሰም፣ በምን ቀለም – በምን ብራና ሊከትበው

(…)

ሰው-አዊ ምስጢራችንን – በምን አቅሙ ሊገልጸው

እኛው ጮኸን – ካልዘከርነው ካልተናገርነው …" ይላል።

ከየካቲት ድሎች ዓድዋ ይድመቅ እንጂ ቅድመ-ዓድዋም ሆነ ድኅረ-ዓድዋ ጦርነት ደማቅ ድሎች ተመዝግበዋል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ በወርኅ የካቲት የግብጽን ወረራ በጉራ፣ የሶማሊያ ጦርነትን በካራማራ፣ ድል ተቀዳጅታለች።

የካቲት 12 ጭፍጨፋ እና የካቲት 23 የዓድዋ ድልን ጨምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የማንነት፣ የሀዘን ሁነቶችና ተፃራሪ ታሪኮችን አስተናግዷል ይኸው ወርሃ የካቲት።

የ1928ቱ የጣሊያን ወረራ በሽሬ፣ በተንቤን እና በአምባራዶም የጦር ሜዳዎች የተከለከለ መርዝ በኢትዮጵያዊያን ላይ ተርከፍክፎ እንዲቃጠሉ መደረጉም የታሪክ ድርሳናት እማኝ ናቸው።

ወርኅ የካቲት በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ታላላቅ አብዮቶች፣ ታላላቅ ድሎች ተከውነውበታል። ለኢትዮጵያ ሕልውና እንደ ክብር የደም ግብር የቀረበበት፣ በየጋራና ሸንተረሩ የትውልድ መስዕዋትነት የተከፈለበት ጊዜ ነው። የካቲት የድልና የዕድል፤ የደምና ገድል ወር ነው። አሳዛኝም፤ አስደሳችም!

የካቲትና የኢትዮጵያ ታሪክ ግንኙነት ድል የተገኘበት፣ መጥፎ ጠባሳዎችንም ያተምንበት ወቅት በመሆኑ ወርኅ የካቲትን በግጥምጥሞሽ የተሞላ፤ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ጋር ተነጥሎ የሚታይ አይደለም።

ወርኅ የካቲት ክስተቶች ዛሬም አልጠፉ። የካቲት ወር 2010 ዓ.ም በኢህአዴግ ላይ የነበሩ አመጾች የተባባሱበትና ፖለቲከኞች ከእሥር የተፈቱበት ነው። የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኃላፊነት ለመልቀቅ ለፓርቲው መልቀቂያ ደብዳቤ ያቀረቡበት ነው።

ለመሆኑ ወርኅ የካቲት የአመፅ፣ የድልና የሃዘን ታሪካዊ ገጾች ባለቤት የመሆኑ ምስጢር ምን ይሆን? የሚለውን ምሁራን የየራሳቸውን መላ ምት ያስቀምጣሉ።

አንዳንዶቹ ወርኅ የካቲት አርሶ አደሩ የሚያርፍበት፣ ወንዞች ከሙላታቸው በጣም ጎድለውና ደርቀው ሰው የሚገናኝበት በመሆኑ እንዲሁም የፆም ወቅት መሆኑ የውጭ ጠላቶች አስልተው እንደሚመጡ ጠቅሰው፤ ለአብነትም በሰንበትና በፆም ወቅት የተደረገውን ዓድዋን ያነሳሉ።

ሌሎቹ ደግሞ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ አርሶ አደር የሆነባት ኢትዮጵያ ካሏት 13 ወራት መካከል ወርኅ የካቲት ለአርሶ አደሩ ጥጋብ፣ ለመንግሥታት ደግሞ የግብር መሰብሰቢያ ወር በመሆኑ ነው ይላሉ። ‘ግብር ገብር፤ አልገብርም’ በሚል ግብግብ የገበሬዎች አመፅ የታየበት ወር መሆኑን በማውሳት።

በሌላ በኩል ወርኅ የካቲት ተማሪዎች ከአንደኛው መንፈቅ ዓመት ወደ ሁለተኛው የሚሸጋገሩበት በመሆኑ ተማሪዎችም ለንቅናቄ ያነሳሳ ወቅት መሆኑን በ1960ዎቹ የተደረገውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመሬት ለአራሹ፣ የዴሞክራሲ፣ የኃይማኖትና የብሔር ጥያቄዎችን ያነሱበትና አብዮት የቀሰቀሱበት እንደነበር የሚገልጹ አሉ።

ከኢትዮጵያ አልፈው እንደ ዓድዋ ያሉ ለጥቁር ሕዝቦች ትግል አብነት የሆኑ ታሪኮች የተፈጸሙበት፣ አብዮት የተካሄደበትና የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ የተወሰነባቸው ክስተቶችን ያስተናገደ ወር እንደሆነ ያነሳሉ።

ወርኅ የካቲት ከኢትዮጵያ አልፎ በአጠቃላይ የመብትና ነፃነት ትግሎች የተስተናገዱበት ሲሆን በአገረ- አሜሪካ ጥቁሮች ለእኩልነትና ነፃነት የታገሉበት ወቅት በመሆኑ የታሪካቸው አካል በማድረግ ያከብሩታል።

ኢትዮጵያ በየካቲት ወር ካሳለፈቻቸው የድል፤ የደምና ገድል ታሪኮች ልትማር፣ ትውልዱም ታሪኩን ሊያውቅ ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም