ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ሩስያ አጋርነታቸውን ለማጠናከር በሚዲያ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ሊያጎለብቱ ይገባል - ሩሲያዊቷ ጋዜጠኛ ዲያና አልካሺም

አዲስ አበባ የካቲት 21/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያና ሩስያ አጋርነታቸውን ለማጠናከር በሚዲያ ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ሊያጎለብቱ እንደሚገባ የሩሲያው ስፑትኒክ ዓለም ዓቀፍ የዜና አገልግሎት የመካከለኛው ምስራቅና የአፍሪካ ልዩ ዘጋቢ ዲያና አልካሺም ተናገረች።

ሩስያዊቷ ጋዜጠኛ ዲያና አልካሺም ለኢዜአ እንደገለጸችው፤ ሩስያና ኢትዮጵያ በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ያላቸው ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር ሆነ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማጠናከር በተለይ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ሚና የላቀ መሆኑን ተናግራለች።

ኢትዮጵያኖች ስለ ሩስያ ያላቸውን ግንዛቤ ለማጠናከር በተመሳሳይ ሩስያኖች ስለ ኢትዮጵያ እውነታውን እንዲያውቁ የመገናኛ ብዙሃን ወሳኝ ናቸው ብላለች።

ቀደም ሲል አፍሪካዊያን ስለ ሩሲያ መረጃዎችን የሚሰሙት በምዕራባዊያን ምንጮች መሆኑን ጠቅሳ አሁን ላይ ሩስያ በዘርፉ ያላትን ተሳትፎ በማጠናከሯ ይህ አዝማሚያ እየተቀረ መሆኑን ተናግራለች።

በተመሳሳይ በአፍሪካም ጠንካራ የመገናኛ ብዙኃን እየተስፋፉ መሆኑን ገልጻ ይህም የአህጉሪቱ እውነታ በትክክለኛው መልኩ እየተዘገበና እየቀረበ መሆኑን ነው ያስረዳችው።

ያም ብቻ ሳይሆን የሩስያና የአፍሪካ አገራት የዘርፉ ግንኙነት እየጎለበተ መምጣቱን ጠቅሳ ለአብነትም ስፑትኒክ ዓለም አቀፍ የዜና አገልግሎት ከኢትዮጵያ አቻው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር የደረሰውን ሥምምነት አንስታለች።

ይህ አይነቱ የሚዲያ ዘርፍ ትብብር የሁለቱን አገራት ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ነው ሩስያዊቷ ጋዜጠኛ ዲያና አልካሺም የገለጸችው።

ጋዜጠኛዋ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ትክክለኛ ዘገባዎችን በመሥራት የበኩሏን ለመወጣት እንደምትሰራ ገልጻለች።

ኢትዮጵያና ሩሲያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና ማኅበራዊ የትብብር ዘርፎች ከአንድ ምዕተ-ዓመት በላይ የዘለቀ የሁለትዮሽ ግንኙነት አላቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም