በድሬዳዋ በግንባታ ላይ ያሉ መሰረተ ልማቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ አስተዳደሩ በትኩረት ሊሰራ ይገባል- የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ በግንባታ ላይ ያሉ መሰረተ ልማቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ አስተዳደሩ በትኩረት ሊሰራ ይገባል- የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር
ድሬዳዋ (ኢዜአ)የካቲት 21/2015--በድሬዳዋ አስተዳደር በዓለም ባንክ እና በመንግስት በጀት እየተገነቡ ያሉ መሠረተ ልማቶች በፍጥነት ወደ አገልግሎት እንዲገቡ አስተዳደሩ በትኩረት መስራት እንዳለበት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ ፕሮጀክቶችን እስከ መጪው ሰኔ ወር ድረስ አገልግሎት ለማስጀመር በቁርጠኝነት እንደሚሠራም ገልጿል።
በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ የተመራ ቡድን በድሬዳዋ ከተማ በዓለም ባንክና በአስተዳደሩ የተቀናጀ በጀት በከተሞች ተቋማዊና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ መርሃግብር የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ መሠረተ ልማቶችን ጎብኝቷል።
የሚኒስቴሩንና የድሬዳዋ አስተዳደር የካቢኔ አባላትን ያካተተው ቡድን የድሬዳዋን የጎርፍ ስጋት ለመቀነስ በመልካጀብዱ ቀበሌ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እየተገነባ ያለውን የጎርፍ መከላከያ ግንብ ተመልክቷል።
እንዲሁም ተጠናቆ ወደ አገልግሎት ያልገባውን የህዝብ መዝናኛ ማዕከል፣ የጌጠኛ መንገድ ግንባታ፣ የዘመናዊ ቄራ ድርጅት፣ የህዝብና የጋራ መፀዳጃ ቤቶች፣ የአረንጓዴ ልማትና የውሃ ፕሮጀክቶችን ቡድኑ ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።
የቡድኑ አባላት ለአገርና ለድሬዳዋ ሁለንተናዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጾ ያለውንና በቅርቡ ወደ ሥራ የገባውን የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና የሥራ እንቅስቃሴን ከተመለከቱ በኋላ ከቀጠናው ሥራ ሀላፊዎች ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።
በተጨማሪም በአንድ ሥራ ፈጣሪ ወጣት የተገነባና የወዳደቁ የውሃ የፕላስቲክ ኮዳዎችን መልሶ ጥቅም ላይ የሚያውለውን ፋብሪካ የቡድኑ አባላት ተመልከተዋል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በጉብኙቱ ወቅት እንደገለፁት፣ በዓለም ባንክ በተገኘ ብድር እና በመንግስት ተጨማሪ በጀት በድሬዳዋ እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች አበረታች ቢሆኑም ፕሮጀክቶቹን በተቀመጠላቸው ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃት ይገባል።
በድሬዳዋ በከተሞች ተቋማዊና የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ መርሐ ግብር ግንባታቸው እየተገባደዱ ያሉ ፕሮጀክቶች በተያዘው ዓመት ተጠናቀው የነዋሪዎችን ጥያቄዎች እንዲመልሱ አስተዳደሩ በትኩረት መከታተል እንዳለበት ሚኒስትሯ አሳስበዋል።
በተለይ በህዝብ መዝናኛ ማዕከላት የከተማዋ ገቢ እንዲያድግና እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር የባለሃብቶችን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶች የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስገኙ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ዕገዛ እንደሚያደርግም ወይዘሮ ጫልቱ አረጋግጠዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው "እየተከናወኑ ያሉት ፕሮጀክቶች ድሬዳዋ ለሥራና ለመኖሪያ ምቹና ተመራጭ ከተማ እንድትሆን ያግዛሉ" ብለዋል።
በተለይ ከተማዋ የምስራቁ የኢትዮጵያ ከፍል የንግድና የኢንዱስትሪ ከተማ የመሆን ጉዞዋን ለማሳካት የመሠረተ ልማቶች ግንባታ አበርክቶው ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ፕሮጀክቶቹን ወደ አገልግሎት ለማስገባት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም አቶ ሀርቢ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የተጠናቀቁና እየተጠናቀቁ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን እስከ መጪው ሰኔ ወር ድረስ አገልግሎት ለማስጀመር በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ገልጸዋል።