በኢህአዴግ ጉባኤ ድርጅቱ የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ የሚያስችሉ ውሳኔዎች ተወስነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኢህአዴግ ጉባኤ ድርጅቱ የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ የሚያስችሉ ውሳኔዎች ተወስነዋል
አዲስ አበባ መስከረም 26/2011 በኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ጉባኤ ድርጅቱ እንዲጠናክር እና የመሪነት ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ የሚያስችሉ ውሳኔዎች መወሰናቸው ተገለፀ። ድርጅቱ ህዝቡ በጉባኤው የተላለፉት ውሳኔዎች እውን እንዲሆኑ ተሳትፎና ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል። የኢህአዴግ 11ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ከመስከረም 23 እስከ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በሀዋሳ ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት ተጠናቋል። በጉባኤው ኢህአዴግ መድረኩን የሚመጥን ቁመና በመላበስና በስኬት በማጠናቀቅ አንድነቱን አጠናክሮ መውጣቱን ገልጿል። የጉባኤውን መጠናቀቅ ተከትሎ ባወጣው ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ ኢህአዴግ ከምንጊዜውም በላይ እንዲጠናከር እና የመሪነት ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ፣ ለአገሪቱ የፈነጠቀው ተስፋ የበለጠ እንዲለመልም የሚያስችሉ ውሳኔዎች አስተላልፎና አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ማጠናቀቁ ተገልጿል። መግለጫው በአገሪቱ ህዝቦች አነሳሽነት ኢትዮጵያ ወደ ለውጥ ምዕራፍ መግባቷን ጠቁሞ የጉባኤው ተሳታፊዎች ለውጡ እንዳይቀለበስ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ከመግባባት ላይ እንደደረሱ ጠቁሟል። ዴሞክራሲን በማስፋት አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እና ምህዳሩን ይበልጥ ለማስፋት የመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ እንዲጠናከር እንደሚሰራም ነው ያስታወቀው። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የዜጎች ሕገ-መንግስታዊ መብቶች መጣስ እንዲቆምና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፤ የማንነት ጥያቄዎችም በህግ አግባብ እንዲፈቱ አቋም ላይ መደረሱንም አመልክቷል። ጉባኤው የኢህአዴግ አባል ብሔራዊ ድርጅቶች ባካሄዱት ጉባኤ አዳዲስ ምሁራን፣ ወጣቶችና ሴቶችን ወደ አመራር ቋት ማስገባታቸውን እንደ ጥንካሬ በመያዝ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በብቃት ለመምራትና ህዝቡን ለመካስ ቃል የተገባበት መሆኑም ተገልጿል። ኢህአዴግ ከአጋር ፓርቲዎች ጋር በመዋሀድ አንድ ሀገራዊ ፓርቲ በመሆን ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት እና የሚታገሉበት የጋራ መድረክ ይሆን ዘንድ የጥናት ሥራዎች መጀመራቸውም እንዲሁ። በመሆኑም እንደ አንድ ህብረ-ብሄራዊና አገራዊ ድርጅት ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ እንዳለ ገልጾ ለዚህ ዓላማ ስኬት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቋል። ምሁራን፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፀጥታ ኃይሎች አገሪቱ የጀመረችው የለውጥ ጉዞ ከዳር እንዲደርስ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጉባኤው ጥሪ አቅርቧል። መላው የአገሪቱ ህዝቦች ለሰላም ለልማትና ለዴሞክራሲ መስፈን ያላቸው ሚና የማይተካ መሆኑን በመጥቀስ ለዘላቂ ሠላምና የመደመር መርሆዎችና እሴቶችን በመያዝ በጉባኤው የተላለፉት ውሳኔዎች እውን ለማድረግ ሁለንተናዊ ተሳትፎና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል። ሙሉ የአቋም መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል =========================== የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ “ሀገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል 11ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን በብሄር ብሄረሰቦች መዲና፣ የህብረ ብሄራዊነትና የብዝሃነት መገለጫ እና የኢትዮጵያ ተምሳሌት በሆነችው ውቢቷ ሀዋሣ ከተማ ከመስከረም 23 –25/2011ዓ/ም ለሶስት ተከታታይ ቀናት አካሂዶ በስኬትና በድል አጠናቋል፡፡ የድርጅታችን አባላትና የትግላችን ደጋፊዎች፣ አጋሮቻችን፣ ወዳጆቻችንና መላው የአገራችን ህዝቦች የጀመርነውን ለውጥ አጠናክረን እንድንቀጥል፣ ድርጅታችን ከምንግዜውም በላይ እንዲጠናከር እና የመሪነት ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ፣ የፈነጠቀው ተስፋ የበለጠ እየለመለመ እንዲሄድ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን አስተላልፎና አቅጣጫዎችን አስቀምጦ እንዲጠናቀቅ በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው ታሪካዊ ጉባኤ በስኬት በማጠናቀቅ መድረኩን የሚመጥን ቁመና ተላብሰን፣ እንደ ኢህአዴግ አንድነታችንን አጠናክረን መውጣታችንን ስንገልጽ በከፍተኛ መነሳሳትና ቁርጠኝነት ነው፡፡ 11ኛው መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤያችን ታሪካዊ ነው የሚያሰኙት በርካታ እውነታዎች ቢኖሩም ሁነኛ መገለጫው አገር የመበታተን፣ የአንድ አገር ህዝብ እርስ በርስ የመተላለቅና የድርጅታችን ህልውና የማክተም አደጋ አንዣቦበት ከነበረበት ሁኔታ በማምለጥ የሰላም፣ የይቅርታ፣ የፍቅርና አንድነት ተስፋ በለመለመበት ወሳኝ ወቅት ላይ መሆኑ፤ እንዲሁም ኢህአዴግ ለውጡን በፍጥነት እና በዘለቄታ ይዞ መጓዝ የሚያስችለው ቁመና የሚያላብሱ ውሳኔዎች የተላለፉበት መሆኑ ነው፡፡ በ10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ የተቀመጡ አቅጣጫዎች አፈፃፀም ሪፖርት በመገምገም፣ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታና ለውጡን በብቃት የመምራት አስፈላጊነት ላይ በጥልቀት በመወያየት መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን እንደዚሁም የድርጅታችን የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርት ገምግሞ የቀጣይ ርብርብ አቅጣጫዎችን አስቀምጦ ድርጅቱን እስከቀጣይ ጉባኤ የሚመሩ መሪዎችን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ መርጦ ተጠናቅቋል፡፡ ጉባኤያችን እንደ ድርጅት ህዝቡ የሚጠብቀውን ለውጡን በብቃት፣ በፍጥነት እና በቁርጠኝነት በመምራት ህዝባችንን ከስጋት ማላቀቅ የሚያስችል የሀሳብ አንድነት የፈጠርንበት፣ በችግሮቻችንና በመፍትሄ አቅጣጫዎቹ ላይ ልብ ለልብ ተገናኝተን አንድነት ፈጥረን የወጣንበት ጉባኤ ነው፡፡ ኢህአዴግ ባለፉት ሶስት አስርት በሚጠጉ ዓመታት ያስመዘገብናቸው ስኬቶች እንደተጠበቁ ሆነው የህዝቡን የለውጥ ጥማት ሊያረካ የሚችል ሥራ በሚፈለገው ደረጃ ባለመሰራቱ፣ የዴሞክራሲ ባህል አለመጐልበቱ፣ ምህዳሩ እየጠበበ መምጣቱ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ በሚፈለገው ልክ አለመሠራቱ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በስፋት በመታየታቸው፣ የህዝቡ ፍትሐዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ጐልተው በመውጣታቸው፣ የመሠረተ ልማት ተደራሽነትና ጥራት ችግሮች በመታየታቸው፣ ብልሹ አስተዳደር እየሰፋ በመሄዱ፣ የተደራጀ ሌብነት እየረቀቀና ስር እየሰደደ በመምጣቱ ምክንያት ማህበራዊ መሠረቶቻችንን ጨምሮ በህዝቡ ዘንድ ድርጅታችን ያለው ተዓማኒነት የመሸርሸር አደጋ እንዲጋረጥበት ሆኖ ነበር፡፡ የማታ የማታ ችግሮች እየተደማመሩ መጥተው ወደ ግጭትና አለመረጋጋት ብሎም የአገራችንን ህልውና አደጋ ላይ ወደሚጥል ፖለቲካዊ ቀውስ መግባታችን ይታወቃል፡፡ በዚህም ምክንያት በተፈጠሩ ግጭቶች የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ የዜጐች አካል ተጐድቷል፣ የመንግስትና ህዝብ ንብረት ወድሟል፡፡ የችግሮቹ ምንጮቹም በዋናነት ከእኛ የመሪነት ጉድለት ጋር እንደሚያያዙ ጉባኤው በአጽንዖት ገምግሟል፡፡ ድርጅታችን የተስተዋሉበትን ድክመቶች ለማረምና ሀገራችንን ከጥፋት ለማዳን በሕዝቡ ግፊት ከውስጥ የመነጨ የጥልቅ ተሀድሶ ንቅናቄ ጀምሮ አሁን የምንገኝበት ተሰፋ ሰጪ የለውጥ ምህዋር ውስጥ ገብተናል፡፡ እኛ የ11ኛ የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች እንደ ድርጅት የመጣንበት መንገድ፣ አሁን የምንገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ በጥልቀት በመገምገም በሀገራችን ህዝቦች፣ በአጐራባች ሀገሮች እና በመላው ዓለም ዕውቅና የተቸረው የሀገራችን ጅምር የለውጥ እንቅስቃሴ ጐልብቶ ወደማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል ይህንን ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡
- በሀገራችን ህዝቦች አነሳሽነት እና በኢህአዴግ መሪነት ሀገራችን ወደ ተስፋ ሰጪ የለውጥ ምዕራፍ ገብታለች፡፡ ይህ የለውጥ ምዕራፍ የፈነጠቀው የተስፋ ብርሃን በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ መነቃቃትን ከመፍጠሩም ባሻገር ለዘመናት ተኮራርፈው የዘለቁ ወገኖች እንዲታረቁ፣ የታሰሩ እንዲፈቱና የተለያዩ እንዲገናኙ በማድረግ ብሄራዊ መግባባት ከፍ እንዲል ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳበረከተ በጉባኤያችን ታይቷል፡፡
- በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ በመምጣቱ ምክንያት የሀሳብ ብዙሃነትን በብቃት ያለማስተናገድ፣ የሀሳብና የፖለቲካ አቋም ልዩነቶች በጠላትነት የሚፈረጁበት፣ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች እየሰፉ የመጡበት አገራዊ ሁኔታ ውስጥ የነበርን መሆናችንን የገመገምን ሲሆን ዴሞክራሲን በማስፋት ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ችግሮቻችንን በሰለጠነ መንገድ ተወያይተን ለመፍታት የሚያስችሉ ጅምር እርምጃዎች ተወስደዋል፤ እየተወሰዱም ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ተፈርዶባቸው ማረሚያ ቤት የነበሩ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች፣ ጋዜጠኞችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በይቅርታና በምህረት እንዲፈቱ መደረጉ፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩ ላይ ጥያቄ የሚያስነሱ እና መሻሻል የሚገባቸው ህጐች እንዲሻሻሉ አቅጣጫ መቀመጡ፣ የትጥቅ ትግልን እንደ አመራጭ ወስደው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ቡድኖች ወደ ሠላማዊ ትግል መድረክ መመለስ መጀመራቸው ይበል የሚያሰኝ ተግባር መሆኑን ገምግመናል፡፡
- ህብረ - ብሄራዊ ፌደራላዊ ሥርዓቱ ባልተማከለ አስተዳደር ብሔር - ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ዕድል የሰጠ፣ ህዝቦች በሀገሪቷ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያስቻለ፣ የሀገራችንን አንድነት በጽኑ መሠረት ለመገንባት ብቸኛው አማራጭ እንደሆና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ሀገራዊ አንድነትን ለመፍጠር ወሳኝ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኝ ተገምግሟል፡፡
- የምንገኝበት ወቅት የ2ኛው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችንን ማጠናቀቂያ ዋዜማ እንደመሆኑ በኢኮኖሚው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግር ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችሉ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ፣ ለገበያ የሚያመርቱ አርብቶ እና አርሶ አደሮችና በመደገፍ፣ የመስኖ እና መሰል የግብርና ልማት ስራዎችን በማፋጠን፣ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማትን በመደገፍ፣ በንግድ እና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት፣ ገቢ የመሰብሰብ አቅማችንን በማጠናከር የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ መፍጠር አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑ በጉባኤያችን ላይ በዝርዝር ታይቷል፡፡
- የቀሰቀስነው ለውጥ ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስመዘገበ ያለው በሀገር ውስጥ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በውጭ ዲፕሎማሲ ዘርፍም ጭምር መሆኑን በዝርዝር የገመገምን ሲሆን ከጐረቤት ሀገሮች፤ በተለይም ከቀይ ባህር አካባቢ አገራት ጋር የፈጠርነው ትስስር ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበትና በምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር ሁነኛ ሚና የሚጫወት የሰላም፣ የትብብርና የአንድነት ተስፋ የፈጠረ ግንኙነት መሆኑ በዝርዝር የገመገምን ሲሆን የኢትዮ - ኤርትራ ግንኙነት መታደስ በቅድሚያ ሊጠቀስ የሚገባው መሆኑን፤ እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት ወንድማማች ህዝቦች መካከል ተዘርግቶ የነበረው ጥቁር መጋረጃ መቀደዱን ስኬታማ የዲፕለማሲ ስራ ውጤት መሆኑን እና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገምግመናል፡፡
- በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች አውዳሚ ግጭቶች፣ ሥርዓት አልበኝነት እና የህግ የበላይነትን የሚጥሱ ተግባራት ሲፈፀሙ ይስተዋላል፡፡ በስርዓተ አልበኝነት እና በመንጋ ፍትህ ምክንያት የዜጐች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚጣሱበት ነባራዊ ሁኔታ መኖሩን ጉባኤተኛው ገምግሟል፡፡
- በአገር ደረጃ የተለኮሰው የተሃድሦ እንቅስቃሴ የበለጠ እየጠራ እንዲሄድ፣ መሪው ድርጅታችን ኢህአዴግ ብቃት ያለው አመራር መሥጠት አለበት፡፡ ስለሆነም ድርጅታችን መሠረታዊ ባህሪውን ጠብቆ በውስጡ ያለውን ችግር በሚገባ አጥርቶ እንዲወጣ የተለየ ትኩረት ሰጥቶት መሠራት እንደሚገባውም ተገምግሟል፡፡ ከዚህ አኳያ የኢህአዴግ አባል ብሔራዊ ድርጅቶች ባካሄዱት ጉባኤ አዳዲስ ምሁራን፣ ወጣቶችና ሴቶችን ወደ አመራር ቋት ማስገባት መቻላቸውም በጥንካሬ ተገምግሟል፡፡ ይህ የተጀመረው ድርጅታችንን የማጠናከር ሥራ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በብቃት ለመምራትና ህዝቡን ለመካስ ቃል እንገባለን፡፡