ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በድርቅ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ከ200 ሚሊዬን ብር በላይ ድጋፍ ሊያደርግ ነው

አዲስ አበባ(ኢዜአ) የካቲት 21/2015 የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በድርቅ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ከሁለት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ።

የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ጌታቸው ታአ በድርቅ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የሰብአዊ ተቋሙ ድጋፍ የሚያደርግበትን ሁኔታ በተመለከተ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

“ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ በደቡባዊ እና ደቡብ ምስራቃዊ አካባቢዎች የተከሰተው የድርቅ አደጋ በሰው እና በእንስሳቶች ላይ ያስከተለውና እያስከተለ ያለው ጉዳት አስከፊ እየሆነ ነው” ብለዋል ዋና ፀሐፊው።

ማህበሩ ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የችግሩ ሰለባ የሆኑ ወገኖችን ህይወት ለመታደግ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመተባበር ላለፉት አመታት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አመልክተዋል።

ማህበሩ እ.አ.አ በ2022 በደቡብ ክልል ከንባታ ጠምባሮ እና ጋሞ ዞኖች፣ በኦሮሚያ ክልል ቦረና፣ ባሌ፣ ምስራቅ ባሌ እና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች፤ እንዲሁም በሶማሌ ክልል ሸበሌ፣ ፋፈን እና አፍዴር ዞኖች እንዲሁም ሞያሌ አካባቢን ጨምሮ ለ14 ሺህ 530 አባዎራዎች እና እማወራዎች ከ104 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ነው አቶ ጌታቸው ያመለከቱት።

በአሁኑ ወቅትም ድርቁ በተለይ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች እያስከተለ ካለው ጉዳት አንጻር ከተለያዩ እህት ማኅበራት ጋር በመተባበር የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ ምላሽ ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችለውን ቅድመ ሁኔታ በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በዚህም መሰረት በሶማሌ ክልል፣በኦሮሚያ ክልል እና በሞያሌ በድምሩ ብር 206 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚያወጣ እርዳታ ለመስጠት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

እርዳታው የውሃና የስነ-ንጽህና አገልግሎት፣ በጥሬ ገንዘብ የሚሰጥ ድጋፍ እንዲሁም የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን የሚያጠቃልል መሆኑን በመጠቆም።

በችግሩ መጠን ልክ አስፈላጊውን ሰብአዊ ምላሽ ለመስጠት ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጎን በመሆን ሕብረተሰቡ በማህበሩ ግቢ በመገኘት እና 9400 ላይ OK ብለው በመላክ 1 ብር እንዲለግሱ አቶ ጌታቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ላለፉት 87 አመታት በልዩ ልዩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሰብዓዊ ተግባራት ሲያከናውን የቆየና፣ እያከናወነ የሚገኝ አንጋፋ ማህበር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም