ለውሳኔዎች ተፈጻሚነትና ለሃገር ሰላም የድርሻችንን እንወጣለን.... በኢህአዴግ ጉባኤ ላይ የተገኙ ወጣቶች - ኢዜአ አማርኛ
ለውሳኔዎች ተፈጻሚነትና ለሃገር ሰላም የድርሻችንን እንወጣለን.... በኢህአዴግ ጉባኤ ላይ የተገኙ ወጣቶች
ሀዋሳ መስከረም 26/2011 በ11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ለተላለፉ ውሳኔዎች ተፈጻሚነትና ለሃገር ሰላም የድርሻቸውን እንደሚወጡ በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ የተገኙ ወጣቶች ገለጹ፡፡ የጉባኤውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በበኩላቸው ለሀገራዊ ለውጥና ሰላም የወጣቱ ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ በሃዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ዛሬ በተደረገው የኢህአዴግ 11ኛ ጉባኤ ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የሃዋሳና አካባቢዋ ወጣቶች በጉባኤው ለተላለፉ ውሰኔዎችና አቅጣጫዎች ስኬታማነትና ለሃገር ሰላም የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ ለጉባኤው በሰላም መጠናቀቅ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የከተማዋን ሰላም የማስጠበቅ ሥራ ማከናወኑን የተናገረው ኢያሱ ጀቦል የሃዋሳ ከተማ ወጣት ነው፡፡ ጉባኤው በሰላም ጉዳይ መምከሩና ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሰላምን በማስከበር በኩል ወጣቱ የድርሻውን እንዲወጣ በመጠየቃቸው ከምንጊዜውም በላይ ለህዝብ ሰላም በትኩረት ለመስራት መነሳሳቱን ተናግሯል፡፡ "በማጠናቀቂያ መርሃ ግብሩ ላይ የተካሄደው የሲዳማ አባቶች ባህላዊ የቄጠላ ስርዓትን ስለ ሃገር ሰላምና አንድነት መልዕክት የሚያስተላለፍ በመሆኑ ወጣቶች ለመልዕክቱ ተፈጻሚነት መስራት ይኖርብናል" ብሏል፡፡ ከጉጂ ዞን የመጣው ስንታየሁ ካሳሁን በበኩሉ በጉባኤው የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተላለፉ ውሳኔዎች በቀጣይ በተግባር እንዲረጋገጡ ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ነው የገለጸው፡፡ ጉባኤው ላስተላለፋቸው ውሳኔዎች ተፈጻሚነት ሰላም ወሳኝ በመሆኑ ከእያንዳንዱ ቤት ጀምሮ በተለይ ወጣቱ ለሰላም ትኩረት ስጥቶ መስራት እንዳለበትና እሱም ለእዚህ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡ "ጉባኤው ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች ለሃገር ሰላምና አንድነት ጠቀሜታው የጎላ ነው" ያለው ሌላኛው ወጣት ካሳሁን ዳንጉራ በበኩሉ ለተፈጻሚነቱ ወጣቶች ለሰላም ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው አመልክቷል፡፡ በቅርቡ የጋሞ አባቶችን ተግሳፅና ምክር ሰምተው ከሁከትና ብጥብጥ ለተቆጠቡ የአካባቢው ወጣቶች አድናቆቱን የገለጸው ወጣቱ "በሲዳማም አፊኒን የመሰለ ትልቅ ባህላዊ እርቅ የማብረድ ስርዓትን መጠበቅና መተግበር ይኖርብናል" ብሏል፡፡ ሃዋሳ ዓለም አቀፍ እውቅና ያላት ከተማ በመሆኗ ወጣቱ ሰላሟን ለማደፍረስ ለሚፈልጉ አካላት መጠቀሚያ ሳይሆን ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ተከባብረው የሚኖሩባት ከተማ እንድትሆን የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቋል። በጉባኤው ማጠቃለያ ማርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የሃገሪቱን ለውጥ ቀጣይነት ለማረጋገጥ ድርጅቱ አመራሩን በአዲስ ጉልበትና በወጣት ኃይል ማደራጀቱን ተናግረዋል ፡፡