በአዋጭ የስራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተን ህይወታችንን የመለወጥ ተስፋ ሰንቀናል--ሰልጣኞች - ኢዜአ አማርኛ
በአዋጭ የስራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተን ህይወታችንን የመለወጥ ተስፋ ሰንቀናል--ሰልጣኞች
ባህር ዳር (ኢዜአ) የካቲት 21/2015 በአዋጭ የስራ ዘርፎች ላይ ተሰማርተን ህይወታችንን የመለወጥ ተስፋ ሰንቀናል ሲሉ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባዘጋጀው ስልጠና ላይ የተሳተፉ ሰልጣኞች ገለጹ።
ባንኩ በባህር ዳር ባዘጋጀው ስልጠና ላይ የተሳተፈው ወጣት አምላኬ እሱባለው የቀን ስራ በመስራት ኑሮውን ይመራ እንደነበር አስታውሷል።
አሁን ባንኩ ባመቻቸው ስልጠና የገንዘብ አጠቃቀም፣ የብድር አመላለስና የታክስ አከፋፈል መሰረታዊ ዕውቀት ማግኘቱን ገልጾ፤ "በቀጣይ በዶሮ እርባታ ዘርፍ ተሰማርቼ ራሴንና ሀገሬን ለመለወጥ ትልቅ አቅም ፈጥሮልኛል" ብሏል።
ሌላኛው ሰልጣኝ ወጣት ሰይድ አህመድ በበኩሉ "ዘልማዳዊ በሆነ መንገድ የምሰራው የንግድ ስራ በሳይንሳዊ መንገድ ያልተደገፈ መሆኑን የወሰድኩት ስልጠና ግልጽ አድርጎ አሳይቶኛል" በማለት ገልጿል።
በስልጠናው መሰረት ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን በመጠቀም በአንድ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት ራሱንም ሆነ ሃገሩን ለመጥቀም እንደሚሰራ አስታውቋል።
ሌላኛው ሰልጣኝ አቶ አምሳሉ ደስታ በበኩላቸው ያገኙት ስልጠና በቀጣይ ሰርተው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና ሀገራቸውን መቀየር እንደሚያስችላቸው ጠቁመዋል።
''የመስሪያ ግብዓት ከተሟላልኝ የወሰድኩትን ስልጠና ወደ ተግባር ቀይሬ በአጭር ጊዜ ሰርቼ ከድህነት ለመውጣት ዝግጁ ነኝ'' በማለት ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል በሚገኙ 5 የስልጠና ማዕከላት 16 የስልጠና ጣቢያዎች ከ27 ሺህ 500 በላይ ሰልጣኞች ስልጠናውን ወስደው ማጠናቀቃቸውን የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የባህር ዳር ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ አንማው ገዳሙ ናቸው።
በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የተዘጋጀውን ስልጠና ወስደው ያጠናቀቁ ሰልጣኞች በቀጣይ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በግብርና፣ በቱሪዝምና በአገልግሎት ዘርፎች በመሰማራት ለኢኮኖሚ እድገቱ ሚናቸውን እንዲወጡ ያግዛል።
ስልጠናው በንግድ ስራ ክህሎት፣ በገበያ ልማት፣ በቢዝነስ ፕላን ዝግጅት፣ በፖሊሲ ጥናትና በፋይናንስ ዝግጅትና ትንተና ዕውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ ማስቻሉን ገልጸዋል።
ባንኩም አዋጭ የሆኑ የስራ ዘርፎችን ለይተው በግልም ሆነ በአክሲዮን ተደራጅተውና ቢዝነስ ፕላን አዘጋጅተው ለሚቀርቡ ሰልጣኞች የመስሪያ መሳሪያዎችን ብድር እንደሚያቀርብም አስረድተዋል።