ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በአሰሪና ሰራተኞች መካከል ያለው ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ እንዲሆን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል-የስራና ክህሎት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በአሰሪና ሰራተኞች መካከል ያለው ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ እንዲሆን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል-የስራና ክህሎት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 20/2015 ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በአሰሪና ሰራተኞች መካከል ያለው ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ እንዲሆን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአገር ውስጥ የግል ስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች እና ከሰራተኛና አሰሪ ተወካዮች ጋር የግሉን ዘርፍ ከስራ እድል ፈጠራ ጋር ማስተሳሰር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡
ሚኒስትር ድኤታው ንጉሱ ጥላሁን በዚሁ ወቅት የስራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህንን እድልም በተቀናጀ አግባብ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ነው ያነሱት፡፡

በተለይ ኤጀንሲዎቹ በሰራተኛ እና አሰሪ መካከል የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲኖር በኃላፊነት መሰራት እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡
የአሰሪዎች እና የሰራተኞች መብት እኩል መከበር እንዳለበት የተናገሩት ሚኒስትር ድኤታው፤ ከዚህ አኳያ ኤጀንሲዎቹ በሁለቱ ወገኖች የሚኖረው ግንኙነት ጤናማ እንዲሆን ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ይህን ለማሳለጥ ደግሞ ወቅቱን በሚመጥን መልኩ ዘርፉን የሚመለከቱ መመሪያዎች እንደሚዘጋጁ ጠቁመዋል፡፡
የኤጀንሲ ተወካዮች በበኩላቸው ዘርፉን የሚመለከቱ አንዳንድ መመሪያዎች የግልጸኝነት ችግር እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም መንግስት ከኤጀንሲዎች ጋር ተቀራርቦ መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡