ቀጥታ፡

ወጣቶች የነገዋን ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል-የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን

ደብረ ብርሃን (ኢዜአ) የካቲት 20/2015 ወጣቶች ሀገራዊ ምክክሩ በንቃት በመሳተፍ የነገዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበረሰብ ደርጅቶች ጥምረት በሀገራዊ የምክክር የወጣቶች ተሳትፎ ላይ ያተኮረ ውይይት በደብረ ብርሃን ከተማ እያካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት ሙሐመድ ናስር እንደገለጸው የሀገራዊ የምክክር ሂደት የተሳካ እንዲሆን ወጣቶች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል።

ወጣቶች ለሀሰተኛ ትርክቶች ጆሮ ሳይሰጡ ሰላሟ የተረጋገጠ የነገዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት በግንባር ቀደም ሊተጉ እንደሚገባም አስገንዝቧል።

ወጣት ሙሐመድ እንዳለው ከ10 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በፈዴሬሽኑ ታቅፈው እየሰሩ ሲሆን፤ በሀገራዊ ምክከር ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው።

በዚህም ከሲቨክ ማህበረሰብ ደርጅቶች ምክር ቤት ጋር በሁሉም ክልሎች ወጣቶች በሀገራዊ የምክክሩ ፋይዳ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ወጣቶች በሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር-ቤት የፕሮግራምና ልማት አማካሪ ዶክተር ሞገስ ደምሴ ተናገረዋል።

ምክር ቤቱ ሀገራዊ ምክክሩ የተሳካ እንዲሆን ከሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጋር ተቀናጀቶ ለመስራት ስምምነት መፈፀሙንም ገልጸዋል።

በምክክር የሚያምን ማህበረሰብ በመገንባት የኢትዮጵያን ክብርና ልዕልና ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ይህ ተውልድ አሻራውን የሚያኖርበት እንደሆነም አመልክተዋል።

መላው ኢትዮጵያዊ ወጣት የሀገራዊ ልማትና እድገት የሚረጋገጠው ሰላም ሲሰፍን መሆኑን በመገንዘብ ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በንቃት እንዲሳተፉ አሳስበዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ ወጣት ዮሴፍ አበራ በበኩሉ የሀገራዊ ምክክሩ የሀገሪቱን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ሀገር ለማከም የተዘጋጀ ነው ሲል ገልጿል።

በኢትዮጵያ ወንድማማችነትና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር ከእኔነት የእኛነት አስተሳሰብና አመለካከትን በማጎልበት ኢትዮጵያን አስቀድመን በጋራ እንሰራለን ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም