ወንድም ካሊድ ፋውንዴሽን "ሙስሊም ኤይድ ዩ.ኤስ.ኤ" ከተሰኘ ድርጅት የ11 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደረገለት

የካቲት 20/2015 (ኢዜአ) "ሙስሊም ኤይድ ዩ.ኤስ.ኤ" የተሰኘ ድርጅት ወንድም ካሊድ ፋውንዴሽን የሚያከናውነውን በጎ ተግባር የሚያጠናክርበትን የ11 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡

  ድጋፉንም የሙስሊም ኤይድ ዩ.ኤስ.ኤ ፕሮግራም ዳይሬክተር ናደራ ሸብሊ ለወንድም ካሊድ ፋውንዴሽን መሥራችና ስራ-አስኪያጅ አቶ ካሊድ ናስር አስረክበዋል፡፡

 የፋውንዴሽኑ መሥራችና ስራ-አስኪያጅ አቶ ካሊድ ናስር በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በድጋፍ ከተገኘው ገንዝብ ውስጥ በ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ለ15 አቅመ ደካማ አረጋዊያን የመኖሪያ ቤት ዕደሳት ይከናወናል፡፡ 

በቀሪው 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ደግሞ መጪውን የረመዳን ጾምን አስመልክቶ በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ከአንድ ሺህ በላይ ወገኖች ወርሃዊ የምግብ ፍጆታ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ 

ሙስሊም ኤይድ ድርጅት ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ ሌሎች አካላትም የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 የወንድም ካሊድ ፋውንዴሽን ከ3 ዓመት በፊት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ 150 ወገኖች የመጠለያና የምግብ አገልግሎት በመስጠት የተጀመረ ምግባረ-ሰናይ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም