የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት እንዲፋጠን መንግስት ሙስናና ብልሹ አሰራርን ማስቀረት ይኖርበታል--ባለሃብቶች - ኢዜአ አማርኛ
የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት እንዲፋጠን መንግስት ሙስናና ብልሹ አሰራርን ማስቀረት ይኖርበታል--ባለሃብቶች
ባህርዳር (ኢዜአ) የካቲት20/2015 በአማራ ክልል የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት እንዲፋጠን መንግስት በየደረጃው ያለውን ሙስናና ብልሹ አሰራር ለማስቀረት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ባለሀብቶች ገለጹ።
ባለሃብቱ በዘርፉ ያነሳቸውን ቅሬታዎች ፈጥኖ ለመፍታት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገልጸዋል።
በባህር ዳር ከተማ በተካሄደ የ"ኢትዮጵያ ታምርት" የንቅናቄ መድረክ ከተገኙ ተሳታፊዎች መካከል የስሄል ሜታል ድርጅት ሃላፊ አቶ ቴዎድሮስ አበጋዝ እንዳሉት፣ በክልሉ ኢንቨስትመንት ፈጥኖ እንዲስፋፋ በየደረጃው የሚስተዋለውን ሙስናና ብልሹ አሰራርን ማስወገድ ይገባል።
በየደረጃው ባለሃብቱን የሚያንገላቱ አመራሮችና ባለሙያዎችን ፈትሾ በማስወገድ አገርና ህዝብን ለማሳደግ ቁርጠኛ የሆኑትን ወደፊት ማምጣት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ከመሬት፣ ከብድር እና ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ በባለሀብቱ የሚነሱ ጥያቄዎችን ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መንገድ በመፍታት ዘርፉን ማሳደግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
"ብልሹ አሰራር እና ሙስና ከተወገደ ባለሀብቶች ክልሉንና ኢትዮጵያን እንዲያለሙ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል” ብለዋል።
እንደ ሲሚንቶ ላሉ ትላልቅ ፋብሪካዎችና ለእርሻ ኢንቨስትመንት በልዩ ትኩረት የሚያበድሩ ባንኮች ባለመኖራቸው የሌሎች ኢንዱስትሪዎችን ሃብት በማዘዋወር ለመጠቀም መገደዳቸውን አስረድተዋል።
በመሆኑም ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋትና ተወዳዳሪ ለማድረግ እነዚህና ከሙስና ጋር ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ አቶ ካሳሁን ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው በክልሉ የሚስተዋሉ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በክልልና በዞን ደረጃ የፀረ-ሙስና ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ ነው።
"በአሁኑ ወቅት በየዘርፉ በርካታ ጥቆማዎች በመምጣታቸው ተጨባጭ መረጃን በማፈላለግ፣ በመመርመርና በመፈተሽ አጥፊዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ በትኩረት እየሰራን ነው" ብለዋል።
የፖለቲካ አመራሩና ባለሙያው እጁን አስገብቶ ከተገኘ ከሥራ እስከማባረር የሚደርስ የፖለቲካና የዲስፕሊን ርምጃ በመውሰድ የባለሀብቱን ጥያቄ ለመፍታት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በ"ኢትዮጵያ ታምርት'' የንቅናቄ መድረክ ባለሃብቱ ከመሬት፣ ከብድር፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል እና ከመሳሰሉት ጋር ያነሷቸው ችግሮች አቅም በፈቀደ መጠን ከመጪው ዓመት የኢትዮጵያ ታምርት መድረክ አስቀድሞ ለመፍታት እንደሚሰራም ነው ያመለከቱት።
እያንዳንዱን ኢንዱስትሪ በዘርፉ በሰለጠነ፣ ልምድ ባለው እና በትጉህ አመራር እንዲመራ በማድረግ ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል" ያሉት ደግሞ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ናቸው።
ሚኒስትሩ እንዳሉት “ባለሃብቶች በታማኝነት፣ በዘመድ አዝማድ ለኢንዱስትሪዎች የማይመጥን ሰው መድበው ማሰራታቸው ኢንዱስትሪዎች ውጤታማና ምርታማ እንዳይሆኑ ማድረጉን በጥናት ተረጋግጧል” ብለዋል።
በጥናቱ መሰረት ችግሩን ለመፍታት የሰው ሃይል ስልጠናውን ከዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ጋር በመተባበር እንደሚሰጥ የገለጹት አቶ መላኩ፣ "ባለሃብቶችም የሰው ሃይል ስምሪታቸውን ፈትሸው ማስተካከል ይኖርባቸዋል" ሲሉም ገልጸዋል።