ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ስብስባ ላይ እየተሳተፈች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ስብስባ ላይ እየተሳተፈች ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 20/2015 ኢትዮጵያ ዛሬ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ የተጀመረው 52ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ላይ እየተሳተፈች ነው።
በስብሰባው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጄኔቫ ቢሮ እና በስዊዘርላንድ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው ናቸው።
አምባሳደር ፀጋአብ በጄኔቫ የተመድ ቢሮ ዳይሬክተር ጀነራል ታቲያና ቫሎቫያ የሹመት ደብዳቤያቸውን ባሳለፍነው ሳምንት ማስገባታቸው ይታወሳል።
የምክር ቤቱ ታዛቢ አገር የሆነችው ኢትዮጵያን የወከሉት አምባሳደር ፀጋአብ ነገ በሚኖረው የስብሰባ መርሃ-ግብር ላይ መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
52ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሎ እንደሚጠበቅ በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት 47 አባል አገራት ያሉት የድርጅቱ አጋዥ አካል ነው።